ለሕዳሴ ግድብ አፍሪካዊ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ኬንያ ገለጸች።

130

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 18/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ፣ በግብፅ እና በሱዳን መካከል ያለው ልዩነት ከፍጥጫ ይልቅ በድርድር ሊፈታ እንደሚገባው ኬንያ አስታውቃለች።

ኬንያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙረያ በኢትዮጵያ፣ በግብፅ እና በሱዳን መካከል የሚካሄደው የሦስትዮሽ ድርድር “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች” የሚለው በመርህ ላይ የተመሠረተ ሊሆን እንደሚገባ አስታውቃለች።

የሀገሪቱ የውኃ፣ የሳኒቴሽን እና መስኖ ልማት ሚኒስትር ሲሲሊ ካሪዩኪ ዛሬ (ሰኔ 18 ቀን 2012 ዓ.ም) በኬንያ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለምን በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል። በውይይታቸውም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ መፈለግ የሚለው የኬንያ አቋም የፀና መሆኑን ተናግረዋል።

አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው በኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን መካከል እየተካሄደ ስላለው የሶስትዮሽ ድርድር ገለፃ አድርገውላቸዋል። ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ያለው የአቋም ልዩነትም ሁሉንም እኩል እና ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሁም አሸናፊ በሚያደርግ የመተባበር መርህ ሊካሄድ እንደሚገባው ኢትዮጵያ ጽኑ አቋም እንዳላትም አምባሳደሩ አስረድተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ወጪ ወገንን ከድህነት ለማውጣት የሚሰሩት መሆኑን በመግለጽም ፕሮጀክቱ የቀጣናውን ልማት እና ኢኮኖሚያዊ ውህደት እውን ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም ማስረዳታቸውን በኢትዮጵያ የኬንያ ኤምባሲ አስታውቋል።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ ያሉ ልዩነቶች “አፍሪካዊ መፍትሄዎች ለአፍሪካ ችግሮች” በሚለው መርህ እንዲፈቱ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

Previous articleበጋዜጠኞች እና በጋዜጠኝነት ሙያ ያለውን ጫና ማስቀረትና ዘርፉን ማጎልበት ላይ ጠንክሮ እንደሚሠራ የኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎች ማኅበር አስታወቀ።
Next articleምጣኔ ሀብታዊ ትግል እና ኮሮናቫይረስ