“በተሳሳተ ግንዛቤ ጫካ የወጣችሁ ታዳጊዎች እንደእኔ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ”

6
ደብረ ማርቆስ: ታኅሣሥ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ተማሪ ኃይለማርያም አብይ የአማራን ሕዝብ ነጻ ለማውጣት በሚል ወደ ጫካ ሲወጣ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነበር፡፡
በትምህርቱም ውጤታማ እና በቤተሰቦቹም ኾነ በመምህራኖቹ ጥሩ ደረጃ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቅ እንደነበርም ይናገራል።
ከሁለት ዓመት በፊት የክልሉ ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙ መስሎኝ የምወደውን ትምህርቴን አቋርጨ በስህተት ወደ ትጥቅ ገብቸ ነበር ነው ያለው ተማሪ ኃይለማርያም።
ነገር ግን ሁለት ዓመታትን የተሻገረው የእርስ በእርስ ግጭት የበርካታ ሕጻናትን ህልም የነጠቀ ነው ብሏል። ትውልድ የሚቀረጽባቸው የትምህርት ተቋማትን ያወደመ፣ ማኅበረሰቡን ለውስብስብ ችግር የዳረገ እንደኾነም ተማሪ ኃይለማርያም ተናግሯል፡፡
ትግሉ ለሕገ ወጥ አሠራር የተመቸ እና የግል ሃብት ማካበቻ ስለመኾኑም መስክሯል።
በተለይ በትግል ስም ትምህርት ቤቶች ላልተገባ አላማ መዋላቸው፣ ሕጻናት እንዳይማሩ መደረጉ፣ ለመማር በወጡ ሕጻናት እና ለትውልዱ እውቀትን በሚዘሩ መምህራን ላይ ይደርስ በነበረው ስቃይ እና እንግልት ውስጡ ያዝን እንደነበርም ተናግሯል፡፡
“ከትምህርት ውጭ የኾነ ማኅበረሰብ ከባሕር የወጣ ዓሣ እንደማለት ነው” የሚለው ተማሪ ኃይለማርያም “ወጣቶች ተምረን ሀገራችንን በእውቀት እና በቴክኖሎጂ ማሳደግ ሲገባን በተሳሳተ መንገድ ዋጋ እየከፈልን ነው” ያለው።
ገና በትምህርት ገበታ መቆየት ያለብን ታዳጊ ወጣቶች ያልተገባ የሕይዎት መስዋዕትነት ማስተናገዳችን ተገቢ አለመኾኑንም ተገንዝቤያለሁ ይላል።
በዚህ ሁኔታ የሕዝብን ጥያቄ ማመለስ የማይችል እንደኾነ ተረዳሁ የሚለው ተማሪ ኃይለማርያም መንግሥት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ተቀብሎ ወደ ቤቱ መመለሱን ጠቅሷል።
መንግሥት ዘላቂ ሰላምን በማስፈን የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ በመገንባት እና ሕጻናት ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ መሥራት እንደሚገባም ተናግሯል፡፡
አላማ በሌለው ትጥቅ ትግል የሕዝብ ጥያቄ አይመለስም እና በተሳሳተ ግንዛቤ ጫካ የወጡ ታዳጊዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው እና ትምህርታቸው እንዲመለሱም ጥሪ አድርጓል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleስታሸንፍ ተፈላጊ ትኾናለህ!
Next articleበ456 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ተግባራት እንደሚከናወን ግብርና ቢሮ አስታወቀ።