
ወልድያ፡ ታኅሣሥ 18/2018 ዓ.ም አሚኮ) “የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች” በሚል መሪ መልዕክት የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ከከተማዋ ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ምክክር አድርጓል።
የምክክሩ ተሳታፊዎች እንደሀገር እየተመዘገቡ ያሉ የልማት ትሩፋቶች የኢትዮጵያን ቀጣይ ዕድገት መሠረት አመላካች መኾናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ፣ የጋዝ ምርት መጀመር፣ የኮሪደር ልማት፣ በገበታ ለሀገር እና ሌሎች መንገዶች የተጠናቀቁ እና እየተሠሩ ያሉ ልማቶች የኢትዮጵያን ገጽታ የቀየሩ መኾናቸውን አውስተዋል።
በወልድያ ከተማ እየተሠራ ያለው የከተማ እና የገጠር የኮሪደር ልማት፣ የገበያ ማዕከላት፣ የመንገድ እና የድልድይ መሠረተ ልማት ግንባታ፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ፣ የመብራት፣ የትውልድ ማበልፀጊያ ተቋማት እና ሌሎች ግንባታዎች ከተማዋን በፍጥነት እንድትለማ ያደረጉ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ይህን ሁሉ ልማት በችግር ውስጥ ኾኖ መሥራት መቻሉ የመሪዎችን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ከከተማዋ ዕድገት አኳያ የአውሮኘላን ማረፊያ እና የባቡር ትራንስፖርት ጥያቄዎች በፌዴራል መንግሥት አፋጣኝ መልስ እንዲሰጠውም ጠይቀዋል።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋዬ ገብሬ በሀገር አቀፍ ደረጃም ይሁን በከተማ አሥተዳደር ደረጃ የተሠሩት የልማት ሥራዎች ጅምር ስለመኾናቸው አስገንዝበዋል።
ወደፊት በርካታ ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርጉ ልማቶችን ብልጽግና ይሠራልም ነው ያሉት።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ የባቡር እና የአውሮኘላን ትራንስፖርት ሕዝብ ሲሰለጥን የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በመኾናቸው ፍትሐዊ ናቸው ነው ያሉት።
እንደ ከተማ አሥተዳደር መልስ እስከሚያገኝ ጥያቄውን ለሚመለከተው የፌዴራል አካል እንዲደርስ ይደረጋል ብለዋል።
ወልድያን ማልማት የሚቻለው በአንድ አቅጣጫ ብቻ አይደለም ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ የከተማዋን ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍ የሚያደርግ ሁሉን አቀፍ ልማት እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ይህ ልማት በውስን አቅም የተሠራ ነው፤ ወደፊት ትልልቅ ኘሮጀክቶች በከተማዋ ይሠራሉም ብለዋል።
ለከተማዋ ዕድገት መሪዎች ብቻቸውን ምንም ሊያደርጉ ስለማይችሉ ሕዝባዊ ትብብር እንደሚያስፈልግም አውስተዋል።
በተለይም የከተማዋ ነዋሪ እና ተወላጅ ሁሉ ወደፊት ለሚሠሩት ኘሮጀክቶች በዕውቀቱ፣ በጉልበቱ እና በገንዘቡ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
