የሀገርን ልማት ለማስቀጠል ሰላም ወሳኝ ጉዳይ ነው።

1

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 18/2018 ዓ.ም አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በስድስቱም ክፍለ ከተሞች “የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግሥት ቱሩፋቶች” በሚል መሪ መልዕክት ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ ከዚህ በፊት በተሠሩ ሥራዎች እና በተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች አንፃራዊ ሰላም ማምጣት መቻሉ ተገልጿል። የታየውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ መሥራት እንደሚጠበቅ ተመላክቷል።

በዳግማዊ ምኒልክ ክፍለ ከተማ የማርዘነብ ቀበሌ የሴቶች ተወካይ ብርቱካን በሪሁን የሰላም እጦት ከማንም በላይ ሴቶችን ለችግር ተጠቂ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

የሴቶች የመጀመሪያ ጥያቄ የሰላም ጥያቄ ነው፤ አሁን በከተማዋ ያለው ሰላም ዘላቂ መኾን አለበት ብለዋል።

ይህንን ሰላም ለማስቀጠል ሴቶች ከፍተኛውን ሚና ልንጫወት ይገባል ነው ያሉት፡፡

በተሠሩ ልማቶች ላይ የሴቶች ሚና ጉልህ ድርሻ አለው ያሉት ወይዘሮ ብርቱካን በቀጣይም ልማት እና ሰላምን ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ተናግረዋል።

የዳግማዊ ሚኒልክ ክፍለ ከተማ ወጣት በጎ ፈቃደኛ ጌታሁን ደሴ ማኅበረሰቡ በሰላም እጦት እየተቸገረ ነው ብሏል፡፡

አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም ቢኖርም ከዚህ የተሻለ ሰላም እንዲኖር እና ሕዝቡ የልማት ተጠቃሚ እንዲኾን ወጣቶች ሰፊ ሥራዎችን መሥራት እንዳለባቸው ገልጿል።

ወጣቶች የሰላምን ዋጋ በመገንዘብ ከጸጥታ ኀይሉ ጋር ተቀናጅተው ሰላምን ለማረጋገጥ የበኩላቸውን እየተወጡ መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡

መንግሥትም ኅብረተሰቡ የሚጠይቃቸውን ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

ሰላምን ለማምጣት መንግሥት የሄደበት እርቀት እንዳለ ኾኖ ማኅበረሰቡ ለሰላም ዘብ ሊቆም ይገባልም ነው ያሉት፡፡

የግሽ ዓባይ ክፍለ ከተማ ሰላም በር ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሙሉ ምትኩ እንደሀገር ከድህነት ለመውጣት የሚደረገው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል። ይህንን የሀገር ልማት ለማስቀጠል ሰላም ወሳኝ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

ሰላምን ለማምጣት ጫካ የገቡ ወንድሞች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሕዝባቸው እንዲመለሱም ጠይቀዋል።

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፓለቲካ እና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ጊዜው ታከለ ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችን መፍታት የቀጣይ ወራት የትኩረት አቅጣጫ መኾናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

እነዚህን ተግባራት ወደ ተጨባጭ ሥራ ለመተግበርም መንግሥት የሚጠበቅበትን የማስተባበር፣ ሰላሙን የመጠበቅ፣ ልማቱን የመምራት እና አገልግሎት አሰጣጡን የማሳለጥ ኀላፊነት አለበት ነው ያሉት፡፡

ሕዝቡ ደግሞ በሚችለው መጠን ከመሪዎች ጋር በመኾን በዕውቀት፣ በገንዘብ እና በጉልበት የሚጠበቅበትን ድጋፍ ማድረግ አለበት ብለዋል።

አካባቢውን ተደራጅቶ እንዲጠብቅ፣ የሚሠሩ ሥራዎችን በባለቤትነት እንዲፈጽም እና ሰላምን ለማምጣት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፦ሰናይት በየነ

‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበምዕራብ ጎንደር ዞን ያሉትን ጸጋዎች አሟጦ ለመጠቀም በትኩረት እየተሠራ ነው።
Next articleየወልድያ ከተማን ዕድገት ለማሳለጥ የኅብረተሰቡ ትብብር እና ድጋፍ አስፈላጊ ነው።