
ገንዳ ውኃ፡ ታኅሣሥ 18/2018 ዓ.ም አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር “የጉባ ብስራቶች፣ የመደመር መንግሥት ቱሩፋቶች” በሚል መሪ መልዕክት ከማኅበረሰቡ ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ከለውጡ ዓመታት ወዲህ ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል።
በቀጣይ መንግሥት የሰላም እና ልማት ተግባራትን ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ እንዲሠራ ጠይቀዋል።
ማኅበረሰቡ በአካባቢው በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ተሳትፎውን በማጠናከር የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ብለዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስማረች ቆያቸው ብልጽግና ፓርቲ እንደ ሀገርም ኾነ እንደ አካባቢ ባለፉት ዓመታት በርካታ የልማት ሥኬቶች ማስመዝገብ መቻሉን አውስተዋል።
በከተማዋ በሁሉም ዘርፎች ልማቶችን ለማስቀጠል እና የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ሁሉም ማኅበረሰብ ሰላሙን እያስከበረ ከመንግሥት ጎን በመቆም የልማት አጋር ኾኖ እንዲያግዝ አሳስበዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አብዱልከሪም ሙሐመድ ሕዝብን ያሳተፈ አካታች የልማት ሥራዎችን በማጠናከር ማኅበረሰቡን በሚዛናዊነት እሳቤ ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የማኅበረሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የከተማዋን የዕድገት ጉዞ ለማፋጠን እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ ከለውጡ ወዲህ በዞኑ የአስፋልት መንገድ፣ የመስኖ ፕሮጀክቶች፣ የቴሌ ታዎሮች ግንባታ እና ሌሎች የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።
በልማት ሥራዎች ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግም ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡ ሰላም እና ልማትን ለማስቀጠል ከወዲሁ የትናንቱን አስቸጋሪ ጊዜ በመረዳት ለነገ የተሻለች ሀገር ለመገንባት መሥራት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
በዞኑ በርካታ የውጭ ምንዛሬን የሚያስገኙ ምርቶች፣ የቁም እንስሳት፣ የዕጣን እና ሙጫ ፀጋዎችን አሟጦ ለመጠቀም በትኩረት ይሠራልም ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
