
ደብረ ማርቆስ፡ ታኅሣሥ 18/2018 ዓ.ም አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን በጎዛምን ወረዳ አሥተዳደር የሰላም ጥሪን ተቀብለው ከመጡ የታጣቂ ቡድኑ አባላት ጋር የሰላም የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
የሰላም ጥሪውን ተቀብለው የመጡ የታጣቂ ቡድኑ አባላት ከሁለት ዓመታት በላይ የተሻገረው ግጭት ሕዝብን ለጉስቁልና ከመዳረግ ውጭ ያመጣው ውጤት የለም ብለዋል።
ከተሳሳተ መንገድ በመውጣት ሕዝቡን ለመካስ እና ኅብረተሰቡ ማኅበራዊ እረፍት እንዲያገኝ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ጠቁመዋል።
የተራዘመ ጦርነት የሕዝቡን ስቃይ የሚጨምር በመኾኑ በየጫካው ያሉ ወንድሞች የሰላም ጥሪውን እንዲቀበሉም ጠይቀዋል።
የጎዛምን ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ዓለሙ ውበት የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ሊመለስ የሚችለው ጦርነትን አማራጭ በማድረግ አይደለም፤ ይልቁንም በሰከነ መንገድ ጥያቄዎችን በማቅረብ እና በውይይት ሊኾን ይገባል ነው ያሉት።
ግጭት ሕጻናትን ከትምህርት ገበታ ውጭ አድርጓል፤ ይህ ደግሞ የትውልድ ክፍተትን እየፈጠረ ነው ብለዋል አስተዳዳሪው። በግጭቱ ምክንያት የታጣው ልማት እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ለዘላቂ ሰላም መሥራት ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑን አንስተዋል።
የሰላምን አማራጭ የተቀበሉ ታጣቂዎች በተሳሳተ መንገድ ጫካ የገቡ ኀይሎችን በመምከር የመመለስ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ ከሁለት ዓመታት በላይ ኅብረተሰቡን ለዘርፈ ብዙ ስቃይ እና መከራ የዳረገው ግጭት እንዲያበቃ አስበው የሰላምን አማራጭ ተቀብለው ለመጡ ታጣቂዎች ምሥጋና አቅርበዋል።
ሰላም የሚመጣው ሁላችንም ካለፈው ሰቆቃ እና ከደረሰው ኪሳራ በመማር የበኩላችንን መወጣት ስንችል ነው ብለዋል።
ሌሎች በጫካ ያሉ ኀይሎች መንግሥት በዘረጋው የሰላም መንገድ የሰላምን አማራጭ ተቀብለው እንዲመጡ እና ግጭቱ መቋጫ እንዲያገኝ በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
