ኅብረተሰቡ የሚገድሉ እና የሚዘርፉ ታጣቂዎችን መታገል አለበት።

23

ደብረታቦር፡ ታኅሣሥ 18/2018 ዓ.ም አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ጎንደር ዞን ከጉና በጌምድር ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ የሰላም እና የጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በአካባቢያቸው ሰላም በመጥፋቱ ዝርፊያ፣ እገታ እና ግድያ መበራከቱን አንስተዋል። መገዳደሉ እንደበዛም ተናግረዋል።

የተመረጠ መንግሥትን በአፈሙዝ መጣል አይቻልም፤ በጫካ ያሉ ኀይሎች ወደ ሰላም መጥተው መወያየት አለባቸው፤ የተጀመሩ ልማቶችን ለማስቀጠልም ሰላም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ዘራፊዎችን እያወቅን ለማጋለጥ አልቻልንም ያሉት ነዋሪዎቹ ግድያ እና ዝርፊያውን ለማስቆም ራሳችን በቁርጠኝነት መታገል አለብን ብለዋል።

የሰላም እጦት ሕዝቡ በችግር እንዲገረፍ እያደረገ መኾኑንም አንስተዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ ዘራፊው ኀይል ሰውን በመግደል ሀገርን ለማጥፋት የተሰለፈ ነው ብለዋል።

ጉና በጌምድር ለሀገር አንድነት እና ልማት ታሪክ የሠሩ ጀግኖች የተፈጠሩበት ነው ያሉት አሥተዳዳሪው
አሁን ላይ ሀገር አፍራሾች ሲንቀሳቀሱበት ሕዝቡ በዝምታ ማየት እንደሌለበት ገልጸዋል።

የተጠየቁም ኾኑ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች የሚጠናቀቁት፣ መንገዶች ተከፍተው የሸቀጥ እንቅስቃሴ የሚኖረው ዘራፊው ኀይል ሲወገድ ነው ብለዋል።

ኅብረተሰቡ ለዘራፊው ኀይል ባለመመቸት ሰላሙን ማረጋገጥ እንዳለበትም አንስተዋል።

መንግሥት የሰላም እጁን ዘርግቷል ያሉት አሥተዳዳሪው የሰላም ጥሪውን ባልተቀበለ ኀይል ላይ ግን ሕግን እንደሚያስከብር ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ ትላንት ለሀገረ መንግሥት ምሥረታ እና ለሕግ መከበር ይቆም የነበረ ሕዝብ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር ወግኖ ሀገር የሚያበሳቁልን ቅጥረኛ መታገስ የለበትም ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት የነበረው ዝርፊያ እና ግድያ ከኅብረተሰቡ በወጡ ጽንፈኞች የተፈጸመ መኾኑንም ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ ሰላም ያለውን ዋጋ በመገንዘብም ልጆቹን ወደ ሰላም እንዲመልስ አሳስበዋል። ሰላም በመመኘት ብቻ ስለማይገኝ ኅብረተሰቡ አደረጃጀት ፈጥሮ ለሰላም እንዲነቃነቅም ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ ጠላቶች ጥሬ ሃብቷን በመፈለግ ሰላሟን በማሳጣት ለማተራመስ እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል።

የውስጥ ባንዳዎች ደግሞ በዝርፊያ ለመክበር በተላላኪነት እየሠሩ ነው ብለዋል።

በጫካ የሚገኘው ኀይል የኢትዮጵያ ጠላቶች መሳሪያ ኾኗል ያሉት ኀላፊው የኢትዮጵያን ሰላም እና ልማት ለመጠበቅ መንግሥት ኀላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል።

መንግሥት በአንድ በኩል እያለማ በሌላ በኩል ሕግ እያስከበረ ነው፤ ለዘላቂ ሰላም እና ልማት ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ መታገል ይጠበቅበታል ነው ያሉት። ዘራፊ ኀይሎችን ወደ ሰላም ማምጣት ይጠበቅበታልም ብለዋል።

ሕዝቡ ዘራፊዎችን በመታገል የሰላም እና የልማት ፍላጎቶችን እውን ማድረግ እንዳለበትም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየግዥ ሥርዓቱን ከሙስና እና ብልሹ አሠራር መጠበቅ ይገባል።
Next articleኅብረተሰቡ ማኅበራዊ እረፍት እንዲያገኝ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ተናገሩ።