
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 18/2018 ዓ.ም አሚኮ) የአማራ ክልል የሥነ ምግባር እና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በሥነ ምግባር ግንባታ እና ሙስና መከላከል ዙሪያ የክልል ተቋማት የግዥ ፋይናንስ እና ንብረት አሥተዳደር ዳይሬክተሮች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የአማራ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የግዥ እና ንብረት አሥተዳደር ቡድን መሪ አሸናፊ አስናቀው የግዥ ሥርዓቱን ከሙስና እና ብልሹ አሠራር ለመጠበቅ ሕግን አክብሮ መሥራት እና የግልጽ ጨረታ አሠራርን መተግበር የተሻለ መኾኑን አንስተዋል፡፡
ወደ ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት መግባት ደግሞ የበለጠ ችግሩን ለመፍታት ያግዛል ብለዋል፡፡
የአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የግዥ አሥተባባሪ መጽሔት ሞገስ የግዥ ሥርዓቱን ከብልሹ አሠራር እና ከሙስና የጸዳ ለማድረግ ወደ ዲጂታል ማደጉ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ባለሙያዎችም የተቀመጡ አሠራሮችን ተከትለው በተገቢው መንገድ በመሥራት የመንግሥትን በጀት ለታለመለት ዓላማ ለማዋል መሥራት ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ምክትል ኀላፊ አደራጀው ካሴ በመንግሥት በጀት አሥተዳደር ዙሪያ ከፍተኛውን በጀት የሚይዘው የግዥ እና ንብረት አሥተዳደር መኾኑን ገልጸዋል።
በዚህ ዘርፍ ሙስና እና ብልሹ አሠራርን ለመቅረፍ የተሻሻለ ዲጂታላይዜሽንን ተግባራዊ ማድረግ ላይ የሚያተኩር የግዥ ፋይናንስ እና ንብረት አሥተዳደር አዋጅ መጽደቁን አንስተዋል፡፡
ከኀላፊዎች ጀምሮ ሁሉም ባለሙያዎች የተቀመጡ አሠራሮችን በመተግበር እና ኀላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት ሙስናን መታገል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል የሥነ ምግባር እና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀብታሙ ሞገስ ኮሚሽኑ የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ፣ ብልሹ አሠራር እና ሙስናን ለመከላከል ትኩረት በማድረግ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
በመንግሥት ተቋማት የሚመደበው በጀት ለተገቢው ዓላማ እንዲውል የግዥ ፋይናንስ እና ንብረት አሥተዳደር ባለሙያዎች ሚናቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
እነዚህ ባለሙያዎች የሚያደርጉት የፋይናንስ እንቅስቃሴ ለብልሹ አሠራር የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍ ያለ በመኾኑ የሕጋዊ አሠራር ደኅንነት ማስጠበቅ ላይ ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት።
የግዥ ፋይናንስ እና ንብረት አሥተዳደር በመንግሥት በትኩረት ከተያዙ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ በመኾኑ ዲጂታላይዝድ እንዲኾን እና በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ይፈለጋል ብለዋል።
የዘርፉ ባለሙያዎች ሕግን መሠረት አድርገው በመሥራት የሚታዩ የብልሹ አሠራር እና ሙስና ችግሮችን ለመፍታት ጠንክሮ መሥራት እንደሚያስፈልጋቸውም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
