“ኢትዮጵያ በዘመናዊና አረንጓዴ ትራንስፖርት ዓለምን ለመምራት ዝግጁ ናት” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

10

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያ ብክለት ቀናሽ እንቅስቃሴ (ግሪን ሞቢሊቲ) 2025 ዐውደ ርዕይን ከፍተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በአረንጓዴ የብልጽግና ጉዞ ለትውልዱ ምቹ ሀገር የማስረከብ ጉዟችን በሁሉም መስክ በስኬታማነት ቀጥሏል ብለዋል።

ዛሬ የተከፈተው የኢትዮጵያ ብክለት ቀናሽ እንቅስቃሴ (ግሪን ሞቢሊቲ) 2025 ዐውደ ርዕይና መድረክ ኢትዮጵያ ተፈጥሮን ለመካስና ብክለት ቀናሽ ኢኮኖሚ ለመገንባት የጀመረችው ታሪካዊ ጉዞ ማሳያ መኾኑን ገልጸዋል።

ይህ ዐውደ ርዕይ አዳዲስ የአረንጓዴ ትራንስፖርት ቴክኖሎጂዎች ለዕይታ የሚቀርቡበት ከመኾኑም በላይ፤ በመንግሥት፣ በባለሀብቶችና በኅብረተሰቡ መካከል የጋራ ግንዛቤና ትብብር የሚፈጥር መድረክ ነው ብለዋል።

ከአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት ለመውጣት እንደ አረንጓዴ ዐሻራና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ማስፋፋት ያሉ ውጤታማ የአረንጓዴ ልማት ርምጃዎችን እየወሰድን ነው።

ኢትዮጵያ በዘመናዊና አረንጓዴ ትራንስፖርት ዓለምን ለመምራት ዝግጁ ናት፤ ታዳሽ ኃይልን ከዘመናዊ ትራንስፖርት ጋር በማቀናጀትና የካርበን ልቀትን በመቀነስ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የአረንጓዴ ኢንዱስትሪ ጉዞ ቀዳሚ እያደረግናት እንገኛለን ነው ያሉት።

ለትውልዱ በሁሉም መስክ ምቹ ሀገርን ለማስረከብም የአረንጓዴ ብልጽግና ጉዟችንን አጠናክረን ቀጥለናል። ለዚህ ራዕይ መሳካት የመንግሥት ብቻ ሳይኾን የእያንዳንዱ ግለሰብና ተቋም ዘመኑን የመዋጀት የባሕል፣ የአስተሳሰብ ለውጥ እና ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ብለዋል።

እኛ ስለ አረንጓዴ ዕድገት የምንጨነቀው ስለ መጪው ትውልድ ስለምንጨነቅ ነው። መንግሥት ለዚህ ዓላማ ስኬታማነት የመሪነት ሚናውን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢንተርፕራይዞች የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ናቸው።
Next articleየግዥ ሥርዓቱን ከሙስና እና ብልሹ አሠራር መጠበቅ ይገባል።