“የትምህርት ዘርፉ የሁሉም የልማት ሥራዎቻችን መሪ ተግባር ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

8

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በጉባኤው ከመከረባቸው ጉዳዮች መካከል የትምህርት ዘርፉ አንደኛው ነው።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ “የትምህርት ዘርፉ የሁሉም የልማት ሥራዎቻችን መሪ ተግባር ነው” ብለዋል። ሁሉንም የልማት አቅሞች ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል መኾኑንም ተናግረዋል።

የትምህርት ዘርፉ በጸጥታ እና ከጸጥታ ውጭም ባሉ ምክንያቶች ችግር ውስጥ ያለ ነው ብለዋል። ችግሩን በጋራ ተረባርበን መሻገር አለብን ነው ያሉት። የትምህርት ዘርፉን አስፈጻሚ አካላት ብቻ ሳይኾን ሕግ አውጪውም በተገቢው መንገድ ሊሠራበት እንደሚገባ አመላክተዋል።

በዚህ ዘመን የሥራ ገበያውን መሠረት ያደረገ ጥራት ያለው የሰው ኃይል እያቀረብን ነው ወይ በሚለው ነበር መነጋገር የነበረብን ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ነገር ግን እንዳለመታደል ኾኖ ሕጻናት ትምህርት ቤት ስለ መግባታቸው ነው እየተነጋገርን ያለነው፣ ይህን ወቅቱ የፈጠረብን ችግር ነው ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ በጀት እየመደበ ለትምህርት ቤቶች የግብዓት አቅርቦት እያሟላ መኾኑንም ተናግረዋል።

ቅድሚያ የሚሰጠው የልማት ዘርፍ በመኾኑ የተጓደለውን ለማሟላት ዝግጁ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት በመጻሕፍት ግብዓት አቅርቦት ለውጥ ማምጣቱን ጠቅሰዋል።

የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል በትኩረት ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ መኾኑን አንስተዋል።

በትምህርት ቤቶች በደረጃ ማሻሻል፣ በጥገና እና በግንባታ ኅብረተሰቡ በስፋት መሳተፍ እንዳለበትም ገልጸዋል።

ከትምህርት ገበታ የራቁ ተማሪዎችን ለመመለስ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል። ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት መመለስ በቀጣይም የሚሠራበት ነው ብለዋል።

የመምህራን ምዘናም በትኩረት እየተሠራበት መኾኑን ገልጸዋል። የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን ግንባታ ማስፋት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።

ልዩ ችሎት ያላቸውን ተማሪዎች የሚያበረታታ ተቋም እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት። የትምህርት ሥልጠናችን የአሁኑን እና የወደፊቱን ገበያ መሠረት ያደረገ መኾን አለበት ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ብቸኛ የሥራ ገበያ የመንግሥት ቅጥር አይደለም፤ ይሄን ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የትምህርት ዘርፉን ቸንክረው የያዙ የጸጥታ ችግሮችን ማቃለል አለብንም ብለዋል። ትምህርት ከግጭቱም በፊት ቅርቃር ውስጥ የገባ ዘርፍ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ይሄን በደንብ ተረድቶ መፈተሽ እና መፍትሔ ማስቀመጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ሌሎች ነገ ለሚኖረው የሥራ ገበያ ራሳቸውን እያዘጋጁ ነው፤ እኛም ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን፤ የነገውን አስቦ እና አደራጅቶ መምራት ይጠይቃል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት እና በጥራት እንዲከናወኑ እየተሠራ ነው።
Next articleኢንተርፕራይዞች የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ናቸው።