
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ጎንደር ዞን ነፋስ መውጫ ከተማ አሥተዳደር እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።
የነፋስ መውጫ ከተማ ነዋሪው ጌታቸው ምኅረት በከተማዋ የፋርማሲ፣ የሆስፒታል ተጨማሪ የሥራ ክፍሎች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ የአጸደ ሕጻናት ትምህርት ቤት እና የውኃ መስመር ግንባታዎች እየተከናወኑ መኾኑን ተናግረዋል።
ግንባታዎቹ የማኅበረሰቡን የልማት ጥያቄ የሚመልሱ መኾናቸውን ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ ለልማት ሥራዎቹ በገንዘብ እና በጉልበት እንደሚደግፍም ተናግረዋል።
የነፋስ መውጫ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ደጀን አከለ ከተማዋ በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ደርሶባት እንደነበር አስታውሰዋል። እነዚያን ተቋማት መልሶ ለመገንባት ጥረት እየተደረገ እንደኾነ ነው የገለጹት።
የተጎበኙት ተቋማት የመልሶ ግንባታው አካል መኾናቸውንም ተናግረዋል። በቀጣይ ግንባታቸውን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ ይሠራል ነው ያሉት። ልማቱን የበለጠ ለማጠናከር ከኅብረተሰቡ ጋር እየተመካከርን ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) በከተማ አሥተዳደሩ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊ እና የመሠረተ ልማት ተግባራት እየለሙ እና እየተጠገኑ ነው ብለዋል።
ከልማት ተግባራት ጎን ለጎን ሰላምን የማስፈን ሥራም በትኩረት እየተሠራ እንደኾነ ተመልክተናል ነው ያሉት። ሕዝቡ ከመንግሥት ጋር በመተባበርም ኾነ በራሱ ተነሳሽነት የልማት ሥራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።
በነበረው ግጭት የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ መገንባት የ25 ዓመቱ እቅድ አካል እንደኾነም ገልጸዋል። በሰሜኑ ጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማልማት እየተሠራ ነው ብለዋል።
አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት እና በጥራት እንዲከናወኑ አቅጣጫ መቀመጡንም ገልጸዋል። የልማት ፕሮጀክቶቻችን የሕዝብ ስለኾኑ በባለቤትነት መንፈስ መሳተፍ ይገባል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
