መንግሥት ከኅብረተሰቡ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ ነው።

8
ፍኖተ ሰላም: ታኅሣሥ 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን የሥራ ኀላፊዎች ከቡሬ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በሰላም እና በልማት ዙሪያ በቁጭ ከተማ ተወያይተዋል።
ነዋሪዎቹ ልጆችን ከትምህርት ገበታ ውጭ በማድረግ የሚፈታ ችግር አለመኖሩን አብራርተዋል። እርስ በእርስ ከመገዳደል በመውጣት ወደ ልማት በመዞር መሥራት እንፈልጋለን ብለዋል ነዋሪዎቹ። መንግሥትም አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የምዕራብ ጎጃም ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓባይ ዓለሙ ታጣቂ ኀይሎችን በማውገዝ እና ለሰላም በመሥራት ፊትን ወደ ልማት መዞር ይገባል ብለዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ የፀጥታ መዋቅሩ ሰላምን ለማስፈን ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ መኾኑን ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመኾን ሰላሙን ወደ ተሟላ ተግባር እንዲሸጋገር መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የፀጥታ ችግሩ ከዚህ የከፋ ውድመት እንዳያደርስ ለሰላም መነሳት ያስፈልጋል ብለዋል። መንግሥት ከኅብረተሰቡ የሚነሱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ለመፍታት እየሠራ መኾኑን አብራርተዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው በመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ ሰላምን ለማስፈን ችግሩን አምኖ የጋራ አቋም መያዝ ያስፈልጋል ብለዋል። ከመገዳደል ማንም የሚያተርፍ ባለመኖሩ ታጣቂዎች ሰላምን ምርጫ እንዲያደርጉ ሁሉም መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
በምክትል ቢሮ ኀላፊ ደረጃ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት አማካሪ ጎሹ ፈንቴ ታጣቂ ኀይሉን መታገል እንደሚገባ ገልጸዋል። ኅብረተሰቡ የሚፈልጋቸውን የልማት ጥያቄዎች እንዲመለሱ ለሰላሙ ሁሉም በጋራ በመቆም መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበእንስሳት ሃብት ልማት የላቀ ውጤት ለማምጣት ትኩረት ተሰጥቷል።
Next articleየፖሊዮ ክትባት የሕጻናትን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስን አስፈላጊ ክትባት ነው።