በእንስሳት ሃብት ልማት የላቀ ውጤት ለማምጣት ትኩረት ተሰጥቷል።

3
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 17/2018 ዓ.ም አሚኮ) አሚኮ በጎንደር ከተማ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው በዶሮ እርባታ፣ በከብት ማድለብ እና በወተት ላም እርባታ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የውኃ፣ የመኖ አቅርቦት፣ የገበያ ትስስር፣ የብድር አቅርቦት እና የማስፋፊያ ቦታ ችግሮች እንዳሉባቸው ገልጸዋል።
በዘርፉ ውጤታማ ለመኾን የከተማ አሥተዳደሩ ሊደግፋቸው እንደሚገባም አንስተዋል።
ይህንን መነሻ በማድረግም የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በከተማዋ እየተከናወኑ ባሉት የእንስሳት ሃብት ልማት፣ የሌማት ቱሩፋት ተግባራት እና በኢንተርፕራይዞች በተነሱ ችግሮች ዙሪያ ለአሚኮ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሌማት ቱሩፋት መርሐ ግብር የእንሥሣት ሃብት ልማት በትኩረት ተይዞ እየተሠራበት ነው ብለዋል። ዘርፉን ለማሳደግ በከንቲባ ኮሚቴ እየተገመገመ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው ከሌሎች አካባቢዎች ተሞክሮ በማምጣት ወደ ሥራ መገባቱንም አንስተዋል። በዚህም በግለሰብ ደረጃ ተበታትነው የሚሠሩትን ወደ ክላስተር በማምጣት የመደገፍ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ለአብነትም በ66 ሚሊዮን ብር የዶሮ ክላስተር ሸድ በመገንባት ለኢንተርፕራይዞች በማሥተላለፍ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል። በዚህም ተመራቂዎች ወደ ሥራው እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል።
በወተት ላም እርባታ፣ በማድለብ እና በንብ ማነብ ዘርፎችም ሦሥት ክላስተሮች ተለይተዋል ነው ያሉት።
በተጨማሪም 33 ሄክታር መሬት በመለየት በዓሣ ማርባት፣ በንብ ማነብ እና በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት በስፋት ለመሥራት በዝግጅት ላይ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የገበያ ትስስር ችግር እንዳይገጥም ከተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር እና ከተቋማት ጋር በማስተሳሰር እየተሠራ ነው ብለዋል።
የእንሥሣት መኖ አቅርቦት ችግርን ለመፍታትም ሁለት ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል።
የብድር አቅርቦት እንዲኖር ከባንኮች ጋር በማሥተሳሰር የብድር አቅርቦት እየተመቻቸ መኾኑን አንስተዋል።
በየክላስተሩ የከርሰ ምድር ውኃን እንዲያስቆፍሩ ድጋፍ በማድረግ የውኃ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግም አመላክተዋል።
በቀጣይም ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት፣ ሸዶችን በመገንባት የሥልጠና፣ የቴክኖሎጅ እና የሙያዊ ድጋፍ በማድረግ በዘርፉ የላቀ ውጤት ለማምጣት የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሃይማኖት አባቶች ሁልጊዜም ስለሰላም ማስተማር ይጠበቅባቸዋል።