
ደሴ: ታኅሣሥ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሰላምና ጸጥታ መምሪያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት ተግባራት አፈጻጻም ላይ ምክክር አካሂዷል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም ለጋራ ሰላም በጋራ መሥራት ከቻልን ሀገራችን ታድጋለች ብለዋል። በማኅበረሰቡ ውስጥ በርካታ ችግሮች አሉ ያሉት ተሳታፊዎቹ የቁማር እና አደንዛዥ ዕፅ ሱስ፣ መጥፎ ሥነ ምግባር፣ መጤ ባሕሎች በወጣቶች ዘንድ ተበራክተዋል ነው ያሉት። እነዚህን አጥፊ ነገሮች በጋራ ማውገዝ፣ መከላከያ እና ወጣቶችን ማስተማር፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ይጠበቃል ነው ያሉት።
የሃይማኖት ተቋማት አባቶችም ተከታዮቻችንን ማስተማር እና መቀራረብ ያስፈልገናል ብለዋል። የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ሰይድ አሊ የሰላም እና የልማት ጉዳይ የመንግሥት ብቻ ባለመኾኑ የሃይማኖት ተቋማት እና አባቶች በትኩረት ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል። ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
በየጊዜው እየተገናኙ ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት መምከር ለከተማዋ ሰላም እና ልማት ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር ተቀራርቦ መሥራት ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ለከተማዋ ሰላም እና ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉ ወጣቶች እንዳሉ ሁሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ትንኮሳ የሚፈፅሙ፣ ፀረ ልማት አጀንዳ የሚያራግቡ ስላሉ ይህንኑ ማውገዝ እና መከላከል እንደሚገባም አሳስበዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የሃይማኖት አባቶች ስለሰላም አንድ ሰሞን ብቻ ሳይኾን ሁልጊዜም ማስተማር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ለከተማዋ ልማት እና ሰላም እንቅፋት የሚኾኑትን መገሰጽ እና ማስተማር አለባቸው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የሃይማኖት ተቋማት በከተማዋ የሰላም እና ልማት ላይ እያደረጉ ያሉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- ከድር አሊ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
