
ሁመራ፡ ታኅሣሥ 16/2018 ዓ.ም አሚኮ) እየተሰጣቸው ያለውን ድጋፍ እና ክትትል በመጠቀም በዓመቱ አጋማሽ ፈተና ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ እየተዘጋጁ መኾናቸውን በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የዳንሻ ቢትወደድ አዳነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናግረዋል።
ወቅቱ ተማሪዎች ለዓመቱ አጋማሽ ፈተና ዝግጅት የሚያደርጉበት ነው። አሚኮም የፈተና ዝግጅቱን ለመቃኘት በዳንሻ ቢትወደድ አዳነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝቷል።
ተማሪ አርሴማ ልጃለም እና ተማሪ አደራጀው ብርሃን ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን ፈተና በጥሩ ውጤት ለመወጣት ራሳቸው ከሚያደርጉት ዝግጅት ባሻገር በመምህራን ድጋፍ እየተደረገላቸው መኾኑን ተናግረዋል።
መምህራኑ የሙከራ ፈተናዎችን በማዘጋጀት ተማሪዎች ለፈተና ያላቸውን ዝግጅት እየመዘኑ መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
ቤተ መጽሐፍት ለ24 ሰዓት ክፍት መኾኑን ያነሱት ተማሪዎቹ የመማሪያ መጻሕፍትን ከማንበብ ባሻገር አጋዥ መጻሕፍትንም በማንበብ ጥሩ ዝግጅት ላይ መኾናቸውን አስረድተዋል።
በትምህርት ቤቱ ከመደበኛው ትምህርት በተጨማሪ የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ብቁ ተማሪዎችን ለማፍራት እየተሠራ መኾኑን መምህር እንዳወቅ አንማው እና የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ዓለምአንተ ማሬ አስረድተዋል።
ትምህርት ቤቱ በአንድ ፈረቃ የሚያስተምር በመኾኑ በሁለተኛው ፈረቃ ተማሪዎቹን በብቃታቸው በመለየት የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ ነው ብለዋል።
ተማሪዎች በፈተናው ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የመማር ማስተማር ሂደቱን የመገምገም እና የመከታተል ሥራ እየተከናወነ መኾኑን የዳንሻ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አምባቸው ንጉሡ ገልጸዋል።
በዚህም በዓመቱ አጋማሽ ፈተና በከተማ አሥተዳደሩ ጥሩ ውጤት እንደሚመዘገብ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ገብረማርያም መንግሥቴ ከተማሪዎች ምዝገባ ጀምሮ የመማር ማስተማር ሂደቱ በታቀደው ልክ እየተከናወነ ነው ብለዋል። ለሁሉም ተማሪዎች እንደየችሎታቸው የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጣቸው መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ለሴት ተማሪዎች የሚሰጠው ልዩ ድጋፍም ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል። የመጻሕፍት ስርጭትን በወቅቱ በማከናወን፣ የቤተ መጻሕፍት አጠቃቀምን በማጠናከር ተማሪዎች ለፈተና ዝግጁ እንዲኾኑ እየተደረገ መኾኑን አስረድተዋል።
እየተደረገ ካለው ጥረት አንጻር በዓመቱ አጋማሽ ፈተና በዞኑ የተሻለ ውጤት ሊመዘገብ እንደሚችል አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ አምሳሉ አሞኘ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
