
ፍኖተሰላም፡ ታኅሣሥ 16/2018 ዓ.ም አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ያሠለጠናቸውን የሰላም አስከባሪ አባላት አስመርቋል።
በምረቃ መርሐግብሩ ላይ የተገኙት በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ ሥልጠናው ሀገርን ከብተና እና ከጉስቁልና ለመታደግ ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር መኾኑን ተናግረዋል።
እስካሁን ሕዝቡ በርካታ ችግሮችን እያሳለፈ ነው፤ ከዚህ በኋላ ግን እፎይታን እንዲያገኝ የሰላም አስከባሪ ተመራቂዎች መሥራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የመከላከያ ሠራዊቱ የጸጥታ መዋቅሩን የማደራጀት ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። በሚሠሩት የሰላም ማረጋገጥ ሥራ የሀገርን አደራ እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል። ሥነ ምግባርን በመላበስ የሕዝብን አደራ ለመጠበቅ መዘጋጀት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዕድሜዓለም አንተነህ የአካባቢው የጸጥታ መዋቅር መልሶ እንዲደራጅ እና አንፃራዊ ሰላም እንዲሰፍን የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ዋጋ መክፈሉን ገልጸዋል።
አሁንም የጸጥታ ችግሩ ሕዝቡን ለምሬት እና ለእንግልት እየዳረገ መኾኑን ተናግረዋል። ተመራቂዎቹ ሕዝቡ የናፈቀውን የሰላም አየር እንዲተነፍስ እና ወደነበረ እንቅስቃሴው እንዲመለስ እንዲሠሩ አሳስበዋል።
ተመራቂ የሰላም አስከባሪ አባላቱ በበኩላቸው በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ሕዝቡ አላስፈላጊ መሰዋዕትነት እየከፈለ መኾኑን አንስተዋል።
ሥነ ምግባርን በመላበስ የተሰጣቸውን የሕዝብ አደራ ከዳር ለማድረስ እንደሚተጉም አብራርተዋል።
ያገኙትን ሥልጠና በመጠቀም የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ተሟላ ሰላም ለማሸጋገር በቁርጠኝነት እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
