በጋዜጠኞች እና በጋዜጠኝነት ሙያ ያለውን ጫና ማስቀረትና ዘርፉን ማጎልበት ላይ ጠንክሮ እንደሚሠራ የኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎች ማኅበር አስታወቀ።

144

የኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎች ማኅበር ህጋዊ እውቅና ማግኘቱን አስታውቋል። በዘርፉ የተሻለ ልምድ ያላቸውና በሃገር ውስጥና በዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ላይ የሚሰሩ ዘጠኝ ሥራ አስፈጻሚ አባላትን መርጦ ነው ወደ ሥራ የገባው።

ማኅበሩ ”የብዙኃን መገናኛ ” ተብሎ በተጠቀሰው ስያሜ መሠረት ጋዜጠኞችን ብቻ ሳይሆን የፎቶና የተንቀሳቃሽ ምስል ሙያተኞችን ጨምሮ የትኛውንም የዘርፉን አካላት በአባልነት አቅፎ እንደሚይዝ ተገልጿል። የቀጣይ ተግባራቱን በተመለከተም ዛሬ በአዲስ አበባ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በኢትዮጵያ የብዙኃን መገናኛ ታሪክ ግማሽ ክፍለ ዘመን ቢያስቆጥርም የሚጠበቅበት ልህቀት ላይ እንዳልደረሰ ማኅበሩ በመግለጫው ጠቅሷል፤ ባለሙያዎቹም ሙያዊ ብቃታቸው እንዳልጎለበተና ጥቅማቸውም እንዳልተከበረ ተነስቷል። ለዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ሁሉንም ሙያተኞች ያካተተ፣ አቅሙን የሚያሳድግና ለመብቱ ጥብቅና የሚቆምለት የሙያ ማኅበር አለመኖሩ በዋና ምክንያትነት ተጠቅሷል።

ማኅበሩ በጋዜጠኞች እና በጋዜጠኝነት ሙያ ያለውን ጫና የማስቀረትና ዘርፉን የማጎልበት ዓላማ ሰንቋል ተብሏል፡፡
የብዙኃን መገናኛ ማኅበሩ ዓላማ ይሳካ ዘንድ ሁሉም አካላትና የዘርፉ ተግባር ግድ የሚላቸው ሁሉ አብረውት እንዲሠሩም ጥሪ አቅርቧል።

ዘጋቢ፡-እንዳልካቸው እባቡ-ከአዲስ አበባ

Previous articleበደሴ ከተማ የተነሳ ድንገተኛ የእሳት አደጋ ከ86 በላይ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎችን ለጉዳት ዳረገ፡፡
Next articleለሕዳሴ ግድብ አፍሪካዊ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ኬንያ ገለጸች።