በእንስሳት ሃብት ልማት ውጤት ማምጣት ተችሏል።

2
ጎንደር: ታኅሣሥ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ መነቃቃትን እያሳየ ነው።
በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሌማት ቱሩፋት መርሐ ግብርን ተከትሎ የወተት ልማት፣ የዶሮ እርባታ፣ የንብ ማነብ እና የከብት ማድለብ ዘርፎች ትኩረት እያገኙ እና ተስፋ የሚሰጡ ተግባራትም እየተከናወኑ ይገኛሉ።
አቶ ዘመነ ሸጋው በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በንብ ማነብ ሥራ ተሠማርተው አግኝተናቸዋል። ሥራውን በ50 ሺህ ብር እንደጀመሩት ተናግረዋል።
ከ70 በላይ ዘመናዊ እና ባሕላዊ የንብ ቀፎዎች አሏቸው። የመሥሪያ ቦታ በመንግሥት እንደተመቻቸላቸው እና ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መኾኑንም ነግረውናል።
ከዘመናዊ ቀፎዎች በዓመት ሦሥት ጊዜ፣ ከባሕላዊ ቀፎዎች ደግሞ በዓመት ሁለት ጊዜ ምርት እንደሚያገኙ ነው የገለጹት።
ባለፈው ዓመት ከ1ሺህ 200 ኪሎ ግራም በላይ ማር አምርተው ለገበያ ማቅረባቸውን ለአብነት ገልጸዋል። ወደ ሥራ በገቡ በአጭር ጊዜ ውስጥም ከ500 ሺህ ብር በላይ ካፒታል መድረስ መቻላቸውንም አንስተዋል።
ዘርፉ አዋጭ መኾኑን ተናግረው ቤተሰባቸውን ከማሥተዳደር አልፎ በጎንደር ከተማ የመኖሪያ ቤት ለመሥራት እንደቻሉም ነው የተናገሩት።
በቀጣይም ዘመናዊ ቀፎዎችን በብዛት በጠቀም ማር በሰፊው ለማምረት እየሠሩ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
በከብት ማድለብ ዘርፍ የተሠማራው ሌላኛው ወጣት ሀውልቱ አዱኛ እንደገለጸው የከብት ማድለብ ሥራው አዋጭ መኾኑን ተናግሯል። ከአባቱ ጋር በመኾን ለሥጋ የሚኾኑ ከብቶችን እያደለቡ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መኾናቸውንም ገልጿል።
የበለጠ ምቹ ሁኔታዎች ቢፈጠሩ በዘርፉ ውጤታማ መኾን እንደሚቻልም ነው የተናገረው።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ መላኩ ደምሌ በከተማ አሥተዳደሩ ለእንስሳት ሃብት ልማት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እየተሠራ ነው ብለዋል። ለዘርፉ የሚኾኑ የክላስተር ቦታዎችን በመለየት እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ለአብነትም 10 ቀበሌዎችን በከብት ማድለብ እና 5 ቀበሌዎችን ደግሞ በንብ ማነብ ዘርፎች መለየታቸውን አንስተዋል።
በንብ ሃብት ልማት 21 ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው በሥራ ላይ መኾናቸውን ተናግረዋል። የድጋፍ እና ክትትል ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleከዚያች ከትርፋማዋ የፍቅር ቀን የምንማረው ቢኖርስ?
Next article“የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የተሳካ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)