
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 15/2018ዓ.ም (አሚኮ) ነገሩ እንድህ ነው። በአውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር 1914 በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ሁሌም በክፉ የሚታወሰው እና አውሮፓ ውስጥ ጀምሮ መላ ዓለምን በሁለት ጎራ ከፍሎ እርስ በእርስ ያጫረሰው አንደኛው የዓለም ጦርነት የጀመረበት ዓመት ነበር፡፡
ሐምሌ 28/1914 ልዑል አርክዱክ ፍራንሲስ ፈርዲናንድ የተባለ የአውስትሮ ሃንጋሪ መንግሥት ዙፋን አልጋ ወራሽ የሰርቢያ ዋና ከተማ ሳራይቮ ላይ በመገደሉ ምክንያት የሚሊዮኖችን ሕይወት በመቅጠፍ እስከ አሁን ተወዳዳሪ ያልተገኘለት እና በሰው ልጆች ታሪክ ላይ ጥቁር ጠባሳን ጥሎ ያለፈው አንደኛው የዓለም ጦርነት የጀመረበት ነው፡፡
ኢምፔርያል ዋር ሙዚየም የተሰኘ ድረ ገጽ እና አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ጦርነቱ ከተነሳበት ዕለት ጀምሮ በመጀመሪያዎቹ 30 ቀናት ብቻ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች እና ሰላማዊ ዜጎች ሕይዎታቸው እንደተቀጠፈ ይነገራል።
ይሁንና የገና በዓል ከመድረሱ በፊትም ጦርነቱ እንዲቆም ብዙዎች ተመኝተው ነበር ይላል መረጃው፡፡
በአንጻሩ ግን ጦርነቱም ተባብሶ ቀጠለ፡፡ ታነንበርግ፣ ማርን እና ፐርስ በተባሉ የጦርነት ግንባሮችም ታይቶ የማይታወቅ ዘግናኝ እልቂትን ያስከተለ ጦርነት እንደተካሄደ ታሪክ መዝግቦት ይኖራል፡፡
ከብዙ ሕይወት መጥፋት በኋላ ታኅሣሥ 24/1914 በፈረንጆቹ የገና ዋዜማ ምሽት ላይ ግን ማንም ይኾናል ብሎ ያላሰበው ውሳኔ አርፎ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።
በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ እጅግ አሰቃቂ የኾነውን መጥፎ ጊዜ በበጎ እንዲታወስ የሚያደርግ ፈጽሞ ያልተጠበቀ ግሩም እና ድንቅ ትዕይንትም ተከስቷል፡፡
እሱም በተቃራኒ ጎራ ተሰልፈው ሲጨፋጨፉ የነበሩ የጀርመን እና የብሪታኒያ ወታደሮች ጠመንጃቸውን እየጣሉ ከየምሽጋቸው ወጥተው አንድ ላይ ተሰባስበው የገና መዝሙርን መዘመር ጀመሩ፡፡
ከሰዓታት በፊት በጠላትነት የጥይት እርሳስ ሲለዋወጡ የነበሩ የስጦታ ዕቃ እንኳን ያልነበራቸው ወታደሮች ለጥይት መከላከያ የለበሱትን የብረት ቆብ እያወለቁ ስጦታ በመለዋወጥ አንዳቸው ለአንዳቸው ያላቸውን ፍቅር ገልጸው እንደነበርም ታሪክ ከትቦታል፡፡
ማታ ላይም አንድ ላይ ተቀምጠው የያዙትን ስንቅ እየበሉ፣ በፍቅር እየተጫወቱ እና እየጨፈሩ የማይታመን በሚመስል ሁኔታ የ1914ቱን የገና በዓል በጋራ አከበሩ ይላል መረጃው፡፡
ይች የገና ዋዜማ ምሽትም በዚያ ሞት በነገሰበት አስከፊው የአንደኛው ዓለም ጦርነት ወቅት በበጎ የሚወሳ ደማቅ ታሪክ የተጻፈባት ልዩ ቀን ኾነች፡፡
የዚህ አስደናቂ ታሪክ ተካፋይ ከነበሩ ወታደሮች መካከል አንዳንዶቹ ለጋዜጦች እና ለፍቅረኞቻቸው ደብዳቤዎች ጽፈው ነበርም ይላል መረጃችን።
ደብዳቤዎች ተፋላሚ ወታደሮች ጦርነቱን አቁመው በዓሉን በጋራ ለማክበር የወሰኑባትን ያችን ልዩ የገና ዋዜማ እና የበዓሉን ውሎ የሚነግሩ የፍቅርን እና ወዳጅነትን ኃያልነት አስረጅ ኾነው ዛሬ ድረስ ዘልቀዋል።
የሰው ልጆች ለሰብዓዊነት ቅድሚያ ከሰጠን ጥላቻ ሊያሸንፈን እንደማይችል እና በፈቃዳችን ከጦርነት ልንወጣ እንደምንችል ትልቅ ማሳያ ኾነዋል፡፡
ወዲህስ በተለያየ ወገን ኾነው ሲታገሉ የነበሩ ወታደሮች አንድ ላይ ሲደሰቱ ከዋሉባት ከዚያች ትርፋማዋ የፍቅር ቀን የምንማረው ይኖር ይሆን?
ልባቸው በጦር ሳይኾን በፍቅር ተማርኮ ጦርነት አቁመው አብረው ለዘመሩ የአንደኛው የዓለም ጦርነት ወታደሮች ልብን በሚሰብረው የአንደኛው የዓለም ጦርነት ጥቁር ታሪክ ውስጥ የሰውነትን ዋጋ ከፍ የሚያደርግ ልብን በደስታ የሚሞላ ዛሬም ድረስ የማይረሳ ድንቅ ትውስታ ጥለውልን አልፈዋል፡፡
ያች ቀን በመጭው የኢትዮጵያ ገና በዓል ዋዜማ ምን አለ ዳግም በተፈጠረች አትሉም እንዴ?
ገናን በደም ሳይሆን በፍቅር እንዳሳለፉት የፍቅር ማሳያ፣ የሁለት ሀገር ተዋጊዎች የፍቅር እና የሰላም ገናን ተመኘን።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
