“አባቶቻችን ጠብቀው ያቆዩልንን ባሕል ለተተኪው ትውልድ የማስቀጠል ኀላፊነት አለበን”

2
ደብረ ብርሃን: ታኅሣሥ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን 17ኛው የባሕል እና ኪነ ጥበባት ፌስቲቫል በደብረ ብርሃን ከተማ እየተካሄደ ነው።
በዚህ ፌስቲቫል ላይ ከተለያዩ የዞኑ ወረዳዎች የመጡ ተሳታፊዎች የአካባቢያቸውን ባሕል የሚገልጹ ምግቦች፣ ጭፍራዎች እና አልባሳትን ጨምሮ የተለያዩ የጥበብ ሥራዎችን እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
በፌስቲቫሉ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ተክለየስ በለጠ ዞኑ የበርካታ ጥበብ መፍለቂ፣ የታሪክ ማኅደር እና ዘርፈ ብዙ መገለጫ ያላቸው ባሕሎች መገኛ መኾኑን አስታውሰዋል፡፡
አባቶቻችን ባሕልን፣ ማንነትን እና ቅርስን ከውጭ ወራሪ ጠብቀው አቆይተውልናል ያሉት ምክትል አሥተዳዳሪው በዘመናችን እኛ የሚጠበቅብን አሻራ እንዳለ ኾኖ የቆየውን የባሕል ሃብቶቻችንን መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
“አባቶቻችን ባሕል በማቆየት፣ ታሪክ በመሥራት እና በመጠበቅ፣ ማኅበረሰባዊ ወግን ያከበረ ማንነት ዋጋ ከፍለው ለእኛ አስተላልፈዋል፤ እነዚህን እሴቶች የእኛ ትውልድ የማስቀጠል ኀላፊነት አለብን” ብለዋል፡፡
የዞኑ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ተዋበች ጌታቸው ከዚህ ቀደም ተደርገው የነበሩ ፌስቲቫሎች የዞኑን ባሕል፣ ወግ፣ ታሪክ እና ጥበብ በማስተዋወቅ ረገድ ፋይዳቸው ጉልህ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በዚህኛውም ዙር የዞኑን የባሕል እና የጥበብ አቅም የበለጠ የሚገልጹ ሁነቶች እየታዩ እየቀረቡም መኾኑን ኀላፊዋ ተናግረዋል፡፡
ፌስቲቫሉ ዛሬን ጨምሮ ለሚቀጥሉት ሦስት ቀናት ቆይታ እንደሚደረግ የተቀመጠው መርሐ ግብር ያሳያል።
ዘጋቢ:- ገንዘብ ታደሰ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየዲጂታል አማራ ስትራቴጅ የአሠልጣኞች ሥልጠና መርሐ ግብር በጎንደር ከተማ ተጀምሯል።
Next articleየተጠባባቂ ጥሪ ማስታወቂያ