የዲጂታል አማራ ስትራቴጅ የአሠልጣኞች ሥልጠና መርሐ ግብር በጎንደር ከተማ ተጀምሯል።

2
ጎንደር: ታኅሣሥ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት ርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት የዲጂታል አማራ ስትራቴጂ የአሠልጣኞች ሥልጠና መርሐ ግብርን በጎንደር ከተማ አስጀምሯል።
‎የአሠልጣኞች ሥልጠናው በጎንደር ቀጣና ለሚገኙ የፓሊ ቴክኒክ አሠልጣኞች እና ሠራተኞች ነው የተዘጋጀው።
‎ዲጂታል አማራ ስትራቴጅ ልዩ ልዩ መረጃዎችን ወደ ሶፍት ኮፒ በመቀየር ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው ያሉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ናቸው።
ምክትል ከንቲባዋ የገቢ፣ የንግድ፣ የጤና እና የትምህርት ተቋማትን ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን አስታውቀዋል።
‎በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለ5 ሚሊዮን ወጣቶች ሥልጠናው እንደሚሰጥ የገለጹት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደሊቨሪ ዩኒት አማካሪ ሞገስ ተኬ ናቸው።
‎ከእነዚህ መካከል120ሺህ ወጣቶች ወደ ሥራ ዓለም እንዲቀላቀሉ፣ ሥራ እንዲፈጥሩ እና በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማስቻልን ታሳቢ ያደረገ ሥልጠና መኾኑን አቶ ሞገስ ‎አብራርተዋል።
‎ሥልጠናው የመማር ማስተማር ሥራውን በዲጂታል አሠራር በማገዝ የበቁ ወጣቶችን ወደ ዓለም ገበያ እንዲቀላቀሉ ማድረግን ጨምሮ የዲጂታል ገበያን ማሳለጥ እንደሚያስችል አማካሪው ጠቅሰዋል።
‎የዲጂታል አማራ ስትራቴጂ ፈፃሚ አካላት የአሠልጣኞች ሥልጠና ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኀላፊ እና የትምህርት እና ሥልጠና ዘርፍ አስተባባሪ አማረ አለሙ ዲጂታላይዜሸንን በአግባቡ ለመተግበር የሚያስችል ሥልጠና መኾኑን አንስተዋል።
‎የመማር ማስተማር ሥርዓቱ ከጠመኔ እና ጥቁር ሰሌዳ የተላቀቀ እንዲኾን እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
‎የሰው ኀይል ከማሠልጠን በተጨማሪ በተመረጡ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የኔትወርክ ዝርጋታ መሠረተ ልማት እንደሚሠራም አስተባባሪው ተናግረዋል።
‎የደባርቅ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ያብባል ሙጨ ወቅቱ የሚጠይቀውን የዲጂታል ክህሎት በአግባቡ ከሥልጠናው እንደሚያገኙ አንስተው የሚገኘውን ዕውቀት በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚገባ አመላክተዋል።
‎‎የጎንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አሠልጣኝ መምህር እስከዳር ወርቁ ተማሪዎቹ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ፈጠራን እንዲያሳድጉ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
‎ፕሮግራሙ ወጣቶች እና ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ሲኾን ለተከታታይ አምስት ቀናት እንደሚቀጥል ተጠቁሟል።
‎ዘጋቢ፦ ማርታ አዱኛ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከ800 ሄክታር በላይ መሬት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ይሠራል።
Next article“አባቶቻችን ጠብቀው ያቆዩልንን ባሕል ለተተኪው ትውልድ የማስቀጠል ኀላፊነት አለበን”