
ደብረ ብርሃን: ታኅሣሥ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር በዘንድሮው የበጋ መስኖ ሥራ ከ4 ሺህ 100 ሄክታር በላይ ማሳ እንደሚለማ አስታውቋል።
ከዚህ ውስጥ 4 ሺህ ሄክታሩ በስንዴ ሰብል የሚሸፈን ነው።
የከተማ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኀላፊ መርሻ አይሳነው እስካሁን 91 በመቶ የሚኾነው ማሳ ታርሶ ለዘር የተዘጋጀ ሲኾን ከ900 ሄክታር በላይ የሚኾነው ደግሞ በትራክተር የታረሰ ነው ብለዋል።
በዚህ ዓመት 22 ትራክተር ጥቅም ላይ ውሏል ያሉት አቶ መርሻ “ቴክኖሎጂ የመጠቀም ልምዱ እያደገ መምጣቱንም” ተናግረዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወርቃለማው ኮስትሬ መስኖ ማልማት እና ተጨማሪ ምርት ማግኘት የአርሶ አደሮች ራስን የመቻል ጉዳይ ብቻ ሳይኾን የሉዓላዊነት ጉዳይ ጭምርም ነው ብለዋል።
የመስኖ ሥራን በየጊዜው በማዘመን የምርት መጠኑንም ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት።
አሚኮ ያናገራቸው አርሶ አደሮች እንደሚሉት በትራክተር መታረሱ ጊዜ እና ገንዘብን ከመቆጠብ አልፎ መሬቱ በደንብ ስለሚታረስ ምርት እንዲሰጥ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ:- ለዓለም ለይኩን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
