ከ470 ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት የሰሜን ሸዋ ዞን የዚህ ዓመት የተፈጥሮ ሃብት ሥራ በንቅናቄ ተጀምሯል።

5
ደብረ ብርሃን: ታኅሣሥ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን የ2018 ዓ.ም የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ማስጀመሪያ በአሣግርት ወረዳ አሥተዳደር በጊናሀገር ቢራዝ ተፋሰስ ተካሂዷል።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኤልያስ አበበ የአሣግርት ወረዳ በተፈጥሮ ሃብት ሥራ ለጎረቤት አካባቢ ተሞክሮ የተወሰደበት እና ውጤታማ ሥራዎች የተሠሩበት ነው ብለዋል።
ይህንን ለማስቀጠል የሰላም እና የተፈጥሮ ሃብት ሥራዎችን በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም አብራርተዋል።
በዞኑ በ2018 ዓ.ም የተፈጥሮ ሃብት ሥራ 1ሺህ 184 ተፋሰሶች ላይ የአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራ እንደሚሠራ የገለጹት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ ታደሰ ማሙሻ ናቸው።
ኀላፊው በአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራው ከ470 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚሳተፉም ተናግረዋል።
በበጋ የሚሠራውን የተፈጥሮ ሃብት ሥራ በክረምት በደን መሸፈን ስለሚገባ ከአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራ ጎን ለጎን የችግኝ ማፍላት ዝግጅት ሥራዎችም እንደሚሠሩ አቶ ታደሰ ገልጸዋል።
የአሳግርት ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አላዩ ብሬ ተፈጥሮን ወደ ነበረችበት ለመመለስ ታሪካዊ ኀላፊነት አለብን ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ የተፈጥሮ ሥነ ምኅዳርን ለመጠበቅ የአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራ ልምዶችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።
በንቅናቄ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ የወረዳው አርሶ አደሮች በተፈጥሮ ሃብት ሥራዎች ተፋሰሶች የውኃ ቋት እየኾኑ በመኾኑ እና ውጤቱን እያዩ በመኾኑ ተግባሩን ባሕል አድርገው እየሠሩ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
በሚሠራው የአፈር እና ውኃ እቀባ ከ49 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍን ሲኾን ከዚህ ውስጥ 17 ሺህ 700 ሄክታር በአዲስ እንደሚለማ ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ዘጋቢ፦ ሥነ ጊዮርጊስ ከበደ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበኤርትራ መንግሥት በቀይ ባሕር አፋር ሕዝቦች ላይ እየደረሰ ያለውን ስልታዊ የዘር ማጥፋት ወንጀል ለማስቆም አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ተቋማት ጫና እንዲያሳድሩ የቀይ ባሕር አፋሮች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ጥሪ አቀረበ።
Next articleየተጠባባቂ ጥሪ ማስታወቂያ