በጎንደር ከተማ በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብሩ የወተት ምርት በ10 ቀበሌዎች እየተተገበረ ነው።

3
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የወተት ምርት በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ውስጥ ካሉት ዘርፎች መካል አንዱ ነው። ዘርፉ የቤተሰብን የኑሮ ደረጃ ከማሻሻሉም አልፎ በወተት ልማት እና በግብይት ሰንሰለት ውስጥ ለሚሳተፉ በርካታ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድልን ይፈጥራል።
ወይዘሮ ቤተልሔም ማሩ በጎንደር ከተማ በወተት ላም ርባታ ዘርፍ ተሰማርተው እየሠሩ አግኝተናቸዋል። በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀው የመንግሥት ሥራ ሳይጠብቁ ከእናታቸው እና ከእህታቸው ጋር ኾነው በማኅበር ተደራጅተው በወተት ልማት
ለመሥራት መምረጣቸውን ተናግረዋል።
ሥራውን የጀመሩት በሁለት ላሞች ሲኾን በአሁኑ ወቅት 80 ከብቶች አሏቸው። በከተማዋ አራት የወተት መሸጫ ማዕከላትን ከፍተው ለከተማዋ ማኅበረሰብ እያቀረቡ ይገኛሉ። ለ50 ሠራተኞችም የሥራ እድል ፈጥረዋል።በቀን እስከ 600 ሊትር ወተት በራሳቸው አቅም በማምረት እንዲሁም ተጨማሪ 300 ሊትር የሚኾን ደግሞ ከሌሎች ግለሰቦች በመረከብ እያቀነባበሩ ለገበያ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል። በዚህም ወተት እና የወተት ተዋጽኦ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም ድርጅታቸውን አስፋፍተው ምርታቸውን ለማሳደግ እቅድ እንዳላቸው ጠቁመዋል።ሌላኛዋ በወተት ላም ርባታ የተሰማሩት ወይዘሮ እስከዳር ብርሃኑ የመንግሥት ሠራተኛ እንደነበሩ ለአሚኮ ተናግረዋል። ወይዘሮ እስከዳር በመኪና አደጋ ምክንያት የመንግሥት ሥራን ሲያቆሙ አራት ላሞችን ገዝተው ወደ ከብት እርባታ ገብተዋል።በአሁኑ ወቅት የሚታለቡ 33 ላሞች አሏቸው። በዚህም በቀን ከእያንዳንዳቸው እስከ 27 ሊትር ወተት እያገኙ ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል። ለ11 ሰዎችም የሥራ እድል መፍጠርም ችለዋል።
በተማሪዎች ምገባ፣ ወላጅ አልባ ለኾኑ እና ለችግረኛ ሕጻናትም ወተት በዝቅተኛ ዋጋ በማቅረብ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።በጎንደር ከተማ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት መምሪያ ኀላፊ መላኩ ደምሌ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብሩ በወተት ምርት በ10 ቀበሌዎች እየተተገበረ እንደሚገኝ አንስተዋል።የከተማ አሥተዳደሩ ከአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ ጋር በመቀናጀት ለዘርፉ ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገ ስለመኾኑም አንስተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሰላምን ለማረጋገጥ ቅድሚያ አንድነትን ማጠናከር ያስፈልጋል።