
ደሴ: ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አመልድ ኢትዮጵያ ከአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር በደሴ ከተማ የማር ኤግዚቢሽን እያካሄደ ነው።
በኤግዚቢሽኑ ላይ ከአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ ዞን በንብ ተኮር የብዙኀን ወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ (ማያ) የታቀፉ የንብ አናቢዎች እየተሳተፉ ነው።
የንብ አናቢዎች የማያ ፕሮጀክት የሥራ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር ባሕላዊ የነበረውን የንብ ማነብ ተግባርን በማዘመን ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንድናመጣ አስችሎናል ብለዋል።
“ንብ እንኳን ማሯ መርዟ ዋጋ እንደሚያወጣ የግንዛቤ ለውጥ አምጥተናል” ነው ያሉት።
በባሕላዊ መንገድ ከቀፎ ከፍተኛው ምርታችን ከ10 ኪ.ግ የማይበልጥ ነበር ያሉት አናቢዎቹ በማያ ፕሮጀክት እስከ 50 ኪ.ግ ማር ማምረት መቻላቸውን ገልጸዋል።
ንብ ተኮር የብዙኀን ወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ (ማያ) ፕሮጀክት በመላ ኢትዮጵያ ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እየተተገበረ የሚገኝ ፕሮጀክት ነው።
አመልድ ኢትዮጵያ በአማራ፣ በአፋር፣ በትግራይ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ፕሮጀክቱን እያስተባበረ መኾኑን የገለጹት በአመልድ ኢትዮጵያ የማያ ፕሮግራም አቀስታ ክላስተር አስተባባሪ ዳንኤል ሰጠ በኢትዮጵያ በ127 ወረዳዎች በአማራ ክልል ደግሞ በ45 ወረዳዎች ፕሮግራሙ እየተተገበረ ነው ብለዋል።
የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተፋዘዘውን የንብ ሴክተር በማነቃቃት ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር መኾኑን አቶ ዳንኤል አንስተዋል።
የሀገሪቱን የማር ምርት በሦስት እጥፍ ማሳደግ፣ የተመረተውን የማር ምርት ጥራት በዓለም አቀፍ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ማድረግ፣ የማር አምራቾቹን ውጤታማነት ማገዝ እንዲኹም የማር ኢንዱስትሪው ራሱን እስከሚችል ለወጣቶች ተጓዳኝ የሥራ እድል መፍጠር ተጨማሪ ዓላማዎች መኾናቸውንም ገልጸዋል።
በዚህ ፕሮጀክት በአቀስታ ክላስተር ማለትም ከሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ ዞን ለተውጣጡ 3 ሺህ ወጣቶች የሥራ እድል መፈጠሩን ያነሱት አቶ ዳንኤል በዚህም ከ250 ሚሊዮን በላይ ብድር መሰራጨቱን አንስተዋል።
በኤግዚቢሽኑም ወጣቶቹ የማር ምርታቸውን ይዘው እየተሳተፉ እንደኾነ ነው ያብራሩት።
የደቡብ ወሎ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የእንስሳት እና እንስሳት ተዋፅኦ ግብይት ቡድን መሪ እብሬ ሰይድ የፕሮጀክቱ በዞኑ ተፈፃሚ መኾን ጥራት ያለው ማርን ለማኅበረሰቡ ከማቅረብ አንፃር ፋይዳው የጎላ መኾኑን አንስተዋል።
ጥራት ያለው ማር ለማኅበረሰቡ ለማቅረብ እና ለአምራቾቹ ቋሚ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እየተሠሩ ባሉ የመንግሥት የገበያ ማዕከላት ቦታ ለመስጠት መታሰቡን ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አበሻ አንለይ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
