ማዕድን አውጪውን በአንድ ጊዜ ሚሊዬነር ያደረገው አጋጣሚ!

315

ታንዛንያዊው ማዕድን አውጪ ግለሰብ በአንድ ጊዜ ሚሊዬነር መሆናቸው ተዘግቧል።

የ52 ዓመቱ ግለሰብ በዘርፉ ሥራ ለዓመታት የደከሙ ዝቅተኛ ነዋሪ ናቸው። ከ30 በላይ ልጆች እንዳሏቸውም ቢቢሲ አስነብቧል። “ይታደሉታል እንጂ …” እንዲሉ አንድ ቀን ግን የዘመናት ድካማቸውን ወደ ተድላ የሚቀይር አጋጣሚ ተፈጠረላቸው።

ዝቅተኛ ነዋሪው ባህላዊ ማዕድን አውጪ 9 ነጥብ 2 እና 5 ነጥብ 8 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ሁለት የከበሩ ማዕድናትን አግኝተው ለሀገሪቱ ማዕድን ሚኒስቴር በማስረከብ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማግኘታቸው ተዘግቧል፡፡ ግለሰቡ ያገኙት “ታንዛናይት” የተባለ ማዕድን በአንድ ጊዜ 15 ኪሎ ግራም ሲገኝ በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ እንደሆነ ተዘግቧል።

የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ የማዕድን አውጪው ግለሰብ ተጠቃሚ መሆን በ 2015 (እ.አ.አ) እርሳቸው ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በማዕድን ኢንዱስትሪው የተደረገው ማሻሻያ ማረጋገጫ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከማሻሻያዎቹ መካከል አነስተኛ የማዕድን አውጪዎች ምርታቸውን መሸጥ የሚችሉባቸውን ማዕከላት ማስተዋወቅን ያጠቃልላል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ። ፕሬዝዳንቱ ለግለሰቡ በስልክ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት እንዳስተላለፉም ዘገባው አመልክቷል።

ከ30 በላይ ልጆች አባት እንደሆኑ የተጠቀሱት ዝቅተኛ ነዋሪው ግለሰብ በአንድ ጊዜ ባለፀጋ መሆናቸው የቤተሰባቸውን ሕይዎት ለመቀየር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በየማነብርሃን ጌታቸው

Previous articleመንግሥት የሠራተኞችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ያደረገውን ጥናት ማጠናቀቁን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታወቀ።
Next articleበአማራ ክልል በ 24 ሰዓታት የኮሮናቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው ሁሉም ከቫይረሱ ነጻ ሆነዋል፡፡