
ጎንደር: ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ”ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የምሁራን ሚና” በሚል መልዕክት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና የአሥተዳደር ሠራተኞች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
ዩኒቨርሲቲዎች ከመማር ማስተማር ባሻገር ፖሊሲ በመቅረጽ ለሀገር ግንባታ መሠረት መኾናቸውን ያስረዱት የጎንደር ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አስራት የኢትዮጵያን መጻኢ እድል ለመወሰን የምሁራን ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል።
ምሁራን ሀገር ከገባችበት ችግር እንድትወጣ የበኩላችን ተወጥተናል ወይ? ብሎ ራስን መጠየቅ ይገባል ያሉት ዶክተር አስራት የሕዝብን ችግር መረዳት እና መፍትሄ ማበጀት እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቀደሙት ዘመናት በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ሚናውን የተወጣ ተቋም መኾኑን ያስረዱት የውይይቱ ተሳታፊዎች ሀገር ችግር ባጋጠማት ወቅትም አጋዥ እንደነበር ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከምርምር እና መማር ማስተማር ሥራው ባሻገር የማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት እየሰጠ እንደኾነም ተሳታፊዎቹ ጠቁመዋል።
የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ለጎንደር ከተማ እድገት በሁሉም ዘርፍ እውቀታቸውን እና ሀሳባቸውን እያዋጡ ነውም ተብሏል።
የሀገር እድገት የሚወሰነው ሰላም ሲረጋገጥ በመኾኑ ታጣቂ ኀይሎች ለሰላም እጃቸውን እንዲዘረጉ መሥራት ከምሁራኑ የሚጠበቅ ጉዳይ መኾኑን ተሳታፊዎቹ አንስተዋል።
ለችግሮች መፍትሄ ለማበጀት ምሁራን አጋዥ ሊኾኑ እንደሚገባ ያመላከቱት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ለሀገረ መንግሥት ግንባታ መሪን የሚያበረታ ትችት ወሳኝ መኾኑን አመላክተዋል።
የምሁራን አቅም የከተማዋ እድገት ላይ አሻራ እያሳረፈ እንደሚገኝ የጠቀሱት አቶ ቻላቸው ስማርት ሲቲ እና ሌሎች ሥራዎች ማሣያ ስለመኾናቸው አንስተዋል።
የሰላም እጦቱ የክልሉን የመልማት እድል እያሳጣ መኾኑን የገለጹት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ለሰላም መስፈን የበኩላችሁን ልትወጡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
ያስተማረን ማኅበረሰብ ማገልገል ከሁሉም ይጠበቃል ያሉት አቶ ቻላቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በጎንደር ከተማ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እገዛ እያደረገ መኾኑንም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ:- ደስታ ካሣ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
