ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ እየሠራ መኾኑን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።

3

ከሚሴ: ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች ጽሕፈት ቤት የታክስ ንቅናቄ መድረክ እና የታማኝ ግብር ከፋዮች እውቅና መርሐ ግብር አካሂዷል።

በመድረኩ የተሳተፉ የከሚሴ ከተማ ግብር ከፋዮች ለአሚኮ በሰጡት ሀሳብ ከነሱ በሚሰበሰበው ገንዘብ በከተማ አሥተዳደሩ የተለያዩ ልማቶች ሲሠሩ በማየታችን ግብራችንን ወድደን እና ፈቅደን በወቅቱ እየከፈልን ነው ብለዋል።

የገቢ ግብር አዋጆች እየተሻሻሉ በመኾኑ በቀጣይ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ገልጸዋል።

የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መሐመድ ጁሀር በ2018 በጀት ዓመት በመደበኛ እና ከአገልግሎት ገቢ 536ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።

እስካሁንም ከሁለት መቶ ሀያ ሶስት ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ እንደተቻለ አስረድተዋል።

በተለያየ ጊዜ የታክስ ግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰው በቀጣይ የግብር አዋጁን በሚተላለፉ ግብር ከፋዮች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ተናግረዋል።

ከተማ አሥተዳደሩ ግብር ከፋዮች ከወረቀት ንክኪ ነፃ በኾነ መንገድ ግብራቸውን ባሉበት ኾነው በስልካቸው እንዲከፍሉ እየተደረገ ነውም ብለዋል።

የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሸሪፍ ቃሲም ከተማ አሥተዳደሩ ከሚያመነጨው ኢኮኖሚ አንፃር ተገቢው ገቢ እየተሰበሰበ አለመኾኑን ጠቅሰው ሁሉንም የገቢ አርዕስቶች አሟጦ በመጠቀም ገቢን በአግባቡ ለመሰብሰብ እየተሠራ መኾኑን አብራርተዋል።

የከተማው ማኅበረሰብ የመልማት ጥያቄ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም የገለጹት ከንቲባው ይህን የመልማት ፍላጎት ማሳካት የሚቻለው በሚሰበሰበው ገቢ በመኾኑ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በወቅቱ ሊከፍሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ አሚናት ሁሴን በበኩላቸው በተያዘው በጀት ዓመት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ የታቀደ መኾኑን ገልጸዋል። እስካሁን 38 በመቶውን ማሳካት እንደተቻለ ጠቅሰዋል።

ግብር ከፋዮች የሚሰበሰበው ገቢ መልሶ ለማኅበረሰቡ ጥቅም የሚውሉ ማኅበራዊ ተቋማት እና መሰረተ ልማቶች የሚሟሉት ከሚከፍሉት ግብር መኾኑን አምነው የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ ሊከፍሉ ይገባል ብለዋል።

በመርሐ ግብሩ በከተማው ለሚገኙ ታማኝ ግብር ከፋዮች እውቅና ተሰጥቷል።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleትምህርት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመሻገር መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየተሠራ ነው።
Next articleየታጣቂ ኀይሎች ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡ ምሁራን ኅላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ። ‎