“ሕዝብ ያለመሪው፤ መሪም ያለሕዝቡ ምንም ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ

2

ደሴ: ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች በወቅታዊ የሰላም እና ልማት ጉዳዮች ላይ ከኮምቦልቻ ከተማ የንግዱ ማኅበረሰብ ጋር እየተወያዩ ነው። በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ፣ በብልጽግና ፓርቲ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሙሉጌታ አቢ እና ሌሎችም የክልሉ እና የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር መሪዎችም በመድረኩ ላይ ተገኝተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የኮምቦልቻ ከተማ ነጋዴዎች እንዳሉት የሚገነባው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ያስዋበ ቢኾንም ከተማዋ ከምታስተናግደው የተሽከርካሪ ብዛት አንጻር በቂ አይደለም። ኮምቦልቻ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚወጡ እና የሚገቡ ምርቶች በር መኾኗን የተገነዘበ የመሠረተ ልማት ግንባታ እንደሚያስፈልጋትም ገልጸዋል።

ኮምቦልቻ ምቹ የንግድ ከተማ መኾኗን የጠቀሱት ነጋዴዎች ከተማዋ “ለልማት መገበር ሥልጡንነት ነው” ብለው የሚያስቡ ነጋዴዎች መገኛ ናት ብለዋል።

ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር ግን የከተማዋን የቀደመ ምቹነት አውኮ አልፏል ነው ያሉት። ይህም ሠርተው የሚያሠሩ እና ለክልሉም ትልቅ አቅም የነበሩ ነጋዴዎች ከከተማዋ እንዲወጡ አድርጓል ነው ያሉት።

አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ገልጸዋል። “ትልቁ ሃብታችን ሰላም ነው” ያሉት ነጋዴዎች ሰላምን ለማወክ የሚንቀሳቀሱትን መከታተል እና በጋራ በመሥራት ለሕግ አጋልጦ መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል። በዚህ ረገድም የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

ታጣቂዎች እየሄዱበት ያለው መንገድ ሕዝብን የሚያንገላታ፤ ለራሳቸውም በአጉል ምኞት ሕይወታቸውን የሚነጥቅ ነው ብለዋል። በመኾኑም መንግሥት የዘረጋውን የሰላም አማራጭ ተጠቅመው ይግቡ ነው ያሉት። ይህ ካልኾነ ግን ሕግ በተሟላ ሁኔታ ይከበር እኛም ከአጥፊ ጎን ሳይኾን ከመንግሥት ጎን ቁመን እናግዛለን ብለዋል።

በጫካ ውስጥ ያሉት ብቻ አይደሉም ሀገር እና ሕዝብን እየበደሉ ያሉት፤ በከተሞች ተቀምጠው እና የመንግሥት አካልም ኾነው የሚላላኩ፤ በሚሰጡት አገልግሎትም ሕዝብን በማማረር እና በመበደል ለአልባሌ አመጽ የሚቀሰቅሱ አሉ ነው ያሉት። የመንግሥትን የሥራ ሰዓት ባለማክበር ተገልጋይን የሚያንገላቱ እና የምሬት ምንጭ ኾነው ሕዝብን ከመንግሥት የሚያቃርኑም አሉ ብለዋል።

ጦርነት የጥይት መጮህ ብቻ አይደለም ያሉት ተሳታፊዎች በአገልግሎት ሕዝብን የሚያስጨንቁ፤ ከተማ ተቀምጠው የማኅበራዊ ሚዲያ የበሬ ወለደ ሽብር የሚፈጥሩ፣ በሙስና እና እጅ መንሻ ድሃውን ሕዝብ የሚበዘብዙ እና መሰል ሰዎች ላይ መንግሥት አስፈላጊውን እርምት እንዲወስድ ጠይቀዋል።

ኮምቦልቻ ለቀጣዩ ወደብ ቱሩፋት ቀድማ የተዘጋጀች፣ ሥልጡን የንግድ ሥርዓት ያላት ከተማ ኾና እንድትገነባም ጠይቀዋል።

የከተማ አሥተዳደሩ መሪዎች ከተማዋን በትኩረት ተከታትለው እየገነቡ ላሉት የኮሪደር ልማት እና ሌሎችም ሰው ተኮር ልማቶች የንግዱ ማኅበረሰብ አመሥግነዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሙሉጌታ አቢ እንዳሉት ሰላም ወዳድ የከተማዋ ሕዝብ ባደረገው ጥረት ሰላም ሰፍኖ ልማቶችም እየተከናወኑ ነው። በተለይም ኮምቦልቻ በኮሪደር ልማት እንድትደምቅ እና ለነዋሪዎቿ እንድትመች ታቅዶ እየተሠራ ነው፤ ተጨባጭ ውጤቶችም ታይተዋል ነው ያሉት።

በከተማ አሥተዳደሩ ውስጥ የተሳለጠ የመንግሥት አገልግሎት እንዲኖር እና በአገልግሎት አሰጣጥ ሰበብ ሕዝብን የሚያማርሩ መሪዎችም ኾነ ባለሙያዎችን ለማረምም እየተሠራ ነው ብለዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ ኮምቦልቻ ተወዳዳሪ እና ባለተስፋ ከተማ መኾኗን አንስተዋል። የከተማዋ ነጋዴዎች እና መላው ነዋሪዎች ሰላማቸውን በማስጠበቅ እያከናወኑት ያለው የልማት ሥራም በአርዓያነት የሚወሰድ እና የሚያሥመሠግን ነው ብለዋል።

መንግሥት ከተሞችን ለነዋሪዎቹ ምቹ ለማድረግ በሚሠራው ሥራ ኮምቦልቻም የቱሩፋቱ ተጠቃሚ መኾኗን ተናግረዋል። ኮምቦልቻ የመቻቻል እና የፍቅር ከተማ ናት፣ ሰላምን ለማወክ ለሚጥሩትም ቦታ የላትም፣ ይህንንም በተግባር እያሳየች መኾኗን አብራርተዋል።

ግጭትና ጦርነት ከዚህ በኋላ እንዳይደገም ሁሉም ነጋዴዎች እና ሁሉም ነዋሪዎች አጥፊን ማውገዝ እና ለሰላማቸው መሥራት አለባቸው ነው ያሉት።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ኮምቦልቻ ከተማ የኢንዱስትሪ ማዕከል እንድትኾን በልዩ ትኩረት እየተሠራባት ያለች ባለብዙ ጸጋ ከተማ ናት ብለዋል። በከተማዋ ያለው የአውሮፓላን ማረፊያም ደረጃውን የጠበቀ እንዲኾን እንደሀገር በተሰጠው ትኩረት ዘመናዊ ኾኖ ታድሷል ነው ያሉት።

ኮምቦልቻ ጸጋዋ ብዙ ነው፤ በጸጋዋ ልክ ለምታ የመላው ኢትዮጵያውያን የሥራ፣ የጉብኝት እና የመዝናኛ ከተማ እንድትኾን ደግሞ ሰላምን አረጋግጦ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

“ሕዝብ ያለመሪው፤ መሪም ያለሕዝቡ ምንም ነው” ያሉት አቶ ይርጋ የኮምቦልቻ ከተማ መሪዎች ሕዝባቸውን አክብረው አገልግሎት ይሰጣሉ፣ የሚያጠፋ ካለም ይታረማል ብለዋል። ሕዝቡም ቢኾን ከአገልጋይ መሪዎቹ ጎን በመቆም ለሰላም እና ለልማቱ መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ነግዶ ማትረፍ እና ሃብት ማፍራት የሚቻለው ሰላም ሲሰፍን መኾኑንም ጠቅሰዋል። በመኾኑም የንግዱ ማኅበረሰብ ለሰላሙ ዘብ መቆም እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል። ታጥቀው ጫካ በመውጣት የሕዝብን ልማት የሚያውኩትን መምከር እና ወደሰላም መመለስ የመላው ነዋሪዎች ኀላፊነት መኾን እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለበዓል ወደ ላሊበላ የሚገቡ እንግዶችን ለማስተናገድ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።
Next articleትምህርት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመሻገር መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየተሠራ ነው።