ለበዓል ወደ ላሊበላ የሚገቡ እንግዶችን ለማስተናገድ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።

6

ወልድያ: ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በልደት በዓል ቤዛኩሉን ለመታደም የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስት ወደ ላሊበላ ከተማ በብዛት ይጓዛሉ። የ2018 ዓ.ም የልደት በዓልን የሚታደሙ እንግዶችን ለመቀበል እና ሁለንተናዊ ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲመለሱ ቅድመ ዝግጅት መደረጉ ተገልጿል።

የሰሜን ወሎ ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ገነት ሙሉጌታ ወደ ከተማዋ የሚገቡ እንግዶችን እግር በማጠብ በኢትዮጵያዊ መስተንግዶ የሚቀበሉ የተደራጁ ወጣቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ወጣቶቹ በአራቱም አቅጣጫ የሚገቡ እንግዶችን ይቀበላሉ ብለዋል።

በከተማዋ የሚገኙ ባለኮኮብ ሆቴሎች የውጭ እና የሀገር ውስጥ እንግዶችን ለመቀበል ተዘጋጅተዋል ነው ያሉት።

በዲጂታል ሲስተም አልጋዎች ቀድመው እየተያዙ መሆኑን ኀላፊዋ ገልጸዋል።

አልጋ ቤቶች እና አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል ያሉት ኀላፊዋ ይህን የሚከታተል ግብረኀይል መቋቋሙንም ነው ያስረዱት።

በከተማ ውስጥ ችግሮች እንዳይኖሩ ቁጥጥር የሚያደርጉ ወጣቶች ተደራጅተዋል ነው ያሉት።

ችግሮች ቢፈጠሩ ፍትሕ የሚሰጡ የፖሊስ እና የፍርድ ቤት መዋቅሮች በልዩ አደረጃጀት አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታ ምቹ እንዲኾን መደረጉንም ገልጸዋል።

አስጎብኝዎችም በተረጋጋ ሁኔታ እንግዶችን ተቀብለው ጥሩ ቆይታ እንዲኖራቸው ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ነው ያስረዱት።

የእንግዶችን ጤና ከመጠበቅ አኳያ ማንኛውም እንግዳ የጤና እክል ቢገጥመው ሕክምና የሚያገኝበት ሁኔታ ስለመመቻቸቱም ጠቁመዋል።

ጠንከር ያለ ሕክምና ካስፈለገም በቅዱስ ላሊበላ ሆስፒታል እና ጤና ጣቢያ ሕክምናውን ማግኘት ይችላሉ ነው ያሉት።

የእንግዶች ሙሉ የሕክምና ወጭ በክልሉ ጤና ቢሮ እና በፌዴራል ጤና ሚኒስቴር እንደሚሸፈንም ኀላፊዋ ተናግረዋል።

የላሊበላ ሕዝብ በኢትዮጵያዊ ባሕል እና መልክ እንግዶቹን ለመቀበል ቀናትን እየጠበቀ መኾኑንም ኀላፊዋ ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሙስና ወንጀልን መከላከል የሁሉም ድርሻ ሊኾን ይገባል።