
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የዱር ቤቴ ከተማ አሥተዳደር የልማት ሥራዎችን እና የዱር ቤቴ – ቁንዝላ – ሻውራ – ፍንጅት- ገለጎ -ገንዳ ውኃ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አዲሱ መሐመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችም ተገኝተዋል።
የዱር ቤቴ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ በሪሁን ቢረሳው የዱር ቤቴ ከተማ አሥተዳደር ሰላምን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የልማት ሥራዎችን ሠርቷል ብለዋል።
ዱርቤቴ ከተማ ሰላምን እየጠበቁ ልማትን በማሳለጥ ምሳሌ የሚኾን እንደኾነም አንስተዋል። በዱር ቤቴ ከተማ አሥተዳደር የውኃ እና ፍሳሽ ፕሮጄክት፣ ድልድዮች፣ የቀበሌ ቤቶች ግንባታ እና ሌሎች ተግባራትን መሥራታቸውንም ገልጸዋል።
ዘንድሮም በከተማዋ 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራን ጨምሮ ሌሎች የልማት ሥራዎች እንደሚሠሩ ተመላክቷል። ከተማዋን የማስዋብ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
