በጤና ጣቢያ ደረጃ ከፍተኛ የቀዶ ጥገና ሕክምና ለመስጠት እንደ ክልል ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው።

5

ደባርቅ: ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ ደጃች ሜዳ ጤና ጣቢያ የከፍተኛ ቀዶ ጥገና ሕክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

ለጤና ጣቢያው ሜዲካል ቲምስ ኢንተርናሽናል ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መድሃኒቶችን ጨምሮ የሕክምና አገልግሎት መስጫ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል።

በመርሐ ግብሩ የተገኙት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አበበ ተምትሜ ቢሮው የእናቶች እና ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

“በጤና ጣቢያ ደረጃ ከፍተኛ የቀዶ ጥገና ሕክምናን ማስጀመር ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንጻር እንደ ክልል ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው” ብለዋል።

የሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ልፋት ለማቃለል እና በጤና ጣቢያ ደረጃ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝም አቶ አበበ አመላክተዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ልዑል ብርሃን ከዚህ በፊት የጠለምት ወረዳ ነዋሪዎች የቀዶ ጥገና ህክምናውን ለማግኘት ይቸገሩ እንደነበር ገልጸዋል።

ይሄን ችግር ለማቃለል የሚያስችል የከፍተኛ የቀዶ ጥገና ሕክምና አገልግሎትን በአቅራቢያቸው በሚገኝ ጤና ጣቢያ ማስጀመር መቻሉን ነው የተናገሩት።

በሜዲካል ቲምስ ኢንተርናሽናል የአማራ ክልል ማሥተባበሪያ የጤና እና ሥርዓተ ምግብ ዋና ኀላፊ ዶክተር ሙሉቀን ዘለቀ በወረዳው የሚሰጠውን የሕክምና አገልግሎት ለማሻሻል በሚያስችሉ ተግባርት እየተሳተፉ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም የተጀመረውን የከፍተኛ ቀዶ ጥገና ሕክምና ለማስቀጠል እና ለማጠናከር ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ነዋሪዎች በበኩላቸው የአገልግሎቱ መጀመር ከዚህ በፊት ሕክምና ለማግኘት በተራዘመ መንገድ ምክንያት ሕይወታቸው ያልፍ የነበረን እናቶች እና ሕጻናት ለመታደግ ያስችላል ብለዋል።

በቀጣይም የተሟላ እና ተደራሽ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleነጻ የሕግ ድጋፍ ምንድን ነው?
Next articleከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በዱር ቤቴ ከተማ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ።