ሙስና ዋናው የፍትሕ እጦት መንስኤ ነው።

1
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሙስና ወንጀል በልማት፣ በሰላም እና በመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አለው። በተለዋዋጭ እና ረቂቅ ስልቱ ምክንያትም በቀላሉ ለመከላከል አስቸጋሪ መኾኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያም የአማራ ክልል ፖሊስ ሙስናን ለመከላከል ምን እየሠራ እንደኾነ ጠይቋል።
በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ዋና መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ዳምጤ ባዬ ፖሊስ ሙስናን ለመከላከል ምርመራ አጣርቶ ለፍትሕ እያቀረበ መኾኑን ገልጸዋል።
የሚታዩ የሙስና ዝንባሌዎችን በማቋረጥ የመንግሥት ሃብት ሳይባክን እንዲመለስ እየተሠራ ነው። ከክልል እስከ ወረዳ አጣሪ ክፍል በማቋቋም፣ የአሠራር ሥርዓት በማበጀት እና ምርመራ በማጣራት ለፍትሕ አካሉ እየቀረበ መኾኑንም ተናግረዋል።
በ2018 በጀት ዓመት በአምሥት ወራት ውስጥ 556 የሙስና ጥቆማዎች ቀርበዋል ነው ያሉት፡፡ 401 የምርመራ መዝገቦች ተጣርተውም ለፍትሕ ተልከዋል ብለዋል። 1 ሺህ 119 ተጠርጣሪዎች ምርምራ ተጣርቶባቸዋል ነው ያሉት።
የጠፋ ሃብትንም በማፈላለግ እንዲመለስ ተደርጓል፤ አላግባብ የተሰጠ 106 ሺህ 358 ካሬ ሜትር ቦታ በፍርድ ቤት እንዲታገድ ተደርጓል። በምርመራም ተይዟል ብለዋል።
የመደራጃ ማኅበር መመሪያን ሳያሟሉ ቦታ ሊወስዱ የነበሩ 292 የቤት ማኅበራትም ሂደት እንዲቋረጥ ተደርጓል ነው ያሉት። 1 ሚሊዮን 51 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታም እንዲመለስ ተደርጓል።
64 ሚሊየን 611 ሺህ የመንግሥት ብር ብክነት በፍርድ ቤት ታግዶ እና ተመርምሮ ለፍትሕ መቅረቡን ኮማንደር ዳምጤ ገልጸዋል።
ከፍትሕ ቢሮ፣ ከሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን፣ ከክልሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት እና ከፍትሕ እና አሥተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ጋርም የኦዲት ጉድለትን ለማስመለስ በምክክር እየሠራን ነው ብለዋል።
ጉልህ ጥቆማ በሚቀርብባቸው ተቋማትም በልዩ ኹኔታ በቅንጅት እየተሠራን እንገኛለን ብለዋል።
በክልሉ ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር ለሙስና ምቹ ሁኔታ ኾኗል ነው ያሉት። ችግሩን ለመከላከል ደግሞ እንቅፋት ሊፈጥር እንደሚችልም ተናግረዋል።
የመንግሥት ትኩረት ለጸጥታው ነው በሚል አስተሳሰብ ሙስናን ለመከላከል እና ወደ ሕግ ለማቅረብ እስከ ወረዳ ድረስ ግብረ ኃይል መቋቋሙን ጠቁመዋል። በዚህም የየደረጃው ተቋማት እየተፈተሹ ነው ብለዋል።
ሙስና እና ግጭት ተመጋጋቢ መኾናቸውን የጠቀሱት ኮማንደር ዳምጤ ክልሉ ያጋጠመውን የሰላም ችግር ለመፍታትም ሙስናን ጠንክሮ መከላከል ይጠበቅብናል ብለዋል። በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት እና የፍትሕ ተቋማትም ሙስናን እንዲከላከሉ እና ሕግ እንዲያስከብሩ አሳስበዋል።
በአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች አሥተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ተወካይ ሰብሳቢ አስናቀች ኃይሌ በክልሉ ምክር ቤትም የሙስና መከላከል ሥራ ክትትል እንደሚደረግበት ጠቅሰዋል።
የኦዲት ግኝት ሪፖርት የተደረገባቸው ተቋማት ጉድለቱን እንዲመልሱ እየተደረገ መኾኑን ነው የገለጹት።
የኦዲት ግኝቱ ከአቅም በላይ ኾኖ ማስመለስ ካልተቻለ ለቋሚ ኮሚቴያቸው ተመርቶ ምርመራ እንደሚጣራበት እና ክስ እንደሚመሠረት ነው ወይዘሮ አስናቀች የተናገሩት።
እስካሁን ምርመራ ተጣርቶ ክስ እንዲመሠረትበት የተላከላቸው የኦዲት ጉድለትም ኾነ የሙስና ጉዳይ አለመኖሩን ነው የገለጹት።
“ሙስና ዋናው የሀገር ጸር እና የፍትሕ እጦት መንስኤ ስለኾነ” ሁሉም በየድርሻው ሊታገለው እንደሚገባ ነው ተወካይ ሰብሳቢዋ ያሳሰቡት፡፡
ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleከ700 ሺህ በላይ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ መኾናቸውን የሰሜን ሰሜን ምዕራብ ሪጅን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ።
Next articleበኩር ጋዜጣ ታኅሣሥ 13/2018 ዓ.ም