
ጎንደር: ታኅሣሥ 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአምስቱ የጎንደር ቀጣና ዞኖች እና በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከ700 ሺህ በላይ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ መኾናቸውን የሰሜን ሰሜን ምዕራብ ሪጅን ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል።
ፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ የዜጎችን ተጠቃሚነት በፍትሐዊነት የሚያረጋግጥ እና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን መኾኑን የተናገሩት በሰሜን ሰሜን ምዕራብ ሪጅን ኢትዮ ቴሌኮም የብሔራዊ መታወቂያ አሥተባባሪ ታደሰ ጫቅሉ ናቸው።
የሰሜን ሰሜን ምዕራብ ሪጅን ከባለፈው ዓመት በተሻለ መልኩ በዚህ ዓመት ማኅበረሰቡ ለብሔራዊ መታወቂያ ያለው አመለካከት እየተሻሻለ መምጣቱን አሥተባባሪው ጠቅሰዋል።
ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ማኅበረሰቡ እንዲጠቀም በሁሉም አካባቢ ተደራሽነትን የማስፋት ሥራ እየተከናወነ መኾኑን አሥተባባሪው አብራርተዋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ በምዕራብ ጎንደር ዞን፣ በደቡብ ጎንደር ዞን፣ በሰሜን ጎንደር ዞን እና በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች የዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ ተጠቃሚ መኾናቸው ነው የተናገሩት።
በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ደግሞ ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች ፋይዳ መታወቂያን ማውጣታቸውን የጠቀሱት አሥተባባሪው በአምስቱ ዞኖች እና በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከ700 ሺህ በላይ ዜጎች የዲጂታል ፋይዳ መታወቂያ አገልግሎት ማግኘታቸውን አመላክተዋል።
ተቋሙም የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘዴዎች በመጠቀም በቀጣይም ማኅበረሰቡ የመታወቂያው ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየተሠራ ነው ተብሏል።
አሁን ላይ በሁሉም የአገልግሎት መስጫ ቦታዎች የዲጂታል መታወቂያ መመቻቸቱን አስታውቀው ማኅበረሰቡ ይህን በመረዳት ተጠቃሚ እንዲኾን አሥተባባሪው ታደሰ ጫቅሉ አሳስበዋል።
አገልግሎቱን ሲጠቀሙ ያገኘናቸው ከሰሜን ጎንደር ዞን አዳርቃይ ወረዳ ነዋሪ የኾኑት አቶ አበራ ገብረጻድቅ ፋይዳ መታወቂያ ወጥ የኾነ አሠራርን በመዘርጋት ለዜጎች ደኅንነት እና ለሀገር ምጣኔ ሃብት ወሳኝ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ብሔራዊ መታወቂያ ከአካባቢያዊነት አስተሳሰብ ወጥቶ እንደ ሀገር አንድ የሚያደርገን መኾኑንም አቶ አበራ ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ ነዋሪ የኾኑት ወይዘሮ ዝማም ተስፋዬ በበኩላቸው የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ከፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ጋር እየተሳሰረ በመምጣቱ መታወቂያውን መያዝ የግድ ነው ብለዋል።
የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥም መታወቂያው አስፈላጊ እንደኾነም ወይዘሮ ዝማም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ማኅደር አድማሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
