
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም ሚኒስቴር ሀገራዊ የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያለመ የምክክር መድረክ ከክልል እና ከፌዴራል ምክር ቤቶች ጋር እያካሄደ ነው።
መድረኩ የምክር ቤቶቹ የክትትል እና የቁጥጥር ሕግ በማውጣት ሥራዎቻቸው ላይ የሰላም ግንባታን ማካተት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠር ያለመ ነው።
የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እድሪስ ሰላም ከኅብረተሰቡ ጋር በሥራ ግንባታ እና ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያለ እንጂ ለኾነ ቦታ እና ተቋም የሚሰጥ አይደለም ብለዋል።
ሰላም በሁለንተናዊ ተግባር ውስጥ የሚገኝ እንጂ ሰላም ሚኒስቴር በተናጠል ሊሰጠው የሚችል አይደለም ነው ያሉት። ስለዚህ ሰላምን ለማምጣት በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት በሁሉም ተግባሮቻቸው በሚገባ በማተኮር መሥራት እንደሚኖርባቸውም ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ ሰላምን በተግባር ማምጣት የሚቻለው ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ ሲቻል፣ የተመጣጠነ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ሲኖር እና የእርስ በርስ መተሳሰር ሲኖር ነው ብለዋል።
“ሰላም በመመኘት ብቻ የሚገኝ ሳይኾን” በተግባር ሥራ የሚመጣ እንደኾነ ነው የገለጹት። የምክር ቤት አባላት በክትትል እና ቁጥጥር ሥራቸው እንዲሁም በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሥራዎቻቸው በትኩረት መሥራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
