ከ24 ሺህ በላይ ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ሥራ እና ክህሎት መምሪያ አስታወቀ።

1
ገንዳ ውኃ: ታኅሣሥ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ክህሎት ጽሕፈት ቤት 49ኛ ዙር የኢ ዲ አይ ብድር ከጸደቀላቸው ኢንተርፕራይዞች ጋር የጋራ ውይይት አካሂዷል።
የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ወጣቶች በተሰጣቸው ሥልጠና እና የብድር አግልግሎት በአጭር ጊዜ ሠርተው ለመለወጥ ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የብድር አገልግሎቱን በመጠቀም የተሻለ ሥራ በመሥራት እራሳቸውን እና አካባቢያቸውን ለመጠቅም እንደሚጥሩም አብራርተዋል። መንግሥት ወጣቶችን በልማት ተጠቃሚ እንዲኾኑ የጀመረውን ድጋፍ እና ክትትል አጠናክሮ እንዲቀጥል ወጣቶቹ ጠይቀዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ክህሎት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አዳነ ሀሰን ከ2 ሺህ 400 በላይ ወጣቶችን ቋሚ እና ጊዚያዊ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል። እንደ ከተማ በሁሉም ዘርፍ ወጣቶችን በሥራ ፈጣሪነት ለማሠማራት በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በኢ ዲ አይ ከ350 በላይ ወጣቶችን የብድር አገልግሎት እንዲያግኙ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
ወጣቶችን በዘላቂነት በማቋቋም ተጠቃሚ እንዲኾኑ እንደ ከተማ አሥተዳደር የክትትል እና ድጋፍ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ሥራ እና ክህሎት መምሪያ ኀላፊ ኤፍሬም ወርቁ እንደ ዞን “ከ24 ሺህ በላይ ወጣቶችን በሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን” ገልጸዋል።
በኢ ዲ አይ ከዚህ በፊት ከ1ሺህ 900 በላይ ወጣቶች ተመልምለው በተለያዩ ዘርፎች ሥልጠና የተሰጣቸው መኾኑን አሥረድተዋል። ሥልጠና ከወሰዱት ውስጥ ከ560 በላይ ወጣቶች ብድሩ ጸድቆላቸዋል ብለዋል።
በዞኑ ያሉትን ጸጋዎች በመለየት ሥራ አጥ ዜጎችን ወደ ሥራ ለማሰማራት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ለዞኑ ኢ ዲ አይ ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በማጽደቅ ወጣቶችን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች እንዲሠማሩ እገዛ ያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።
በቀጣይ ለወጣቶች የሥራ መሥሪያ ቦታ እንደሚመቻችላቸውም ኀላፊው አስገንዝበዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ በዞኑ ሰላምን ከማስከበር ጎን ለጎን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን ለማከናወን በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ከልማት ሥራዎች አኳያ ሥራ አጥ ወጣቶችን ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
መንግሥት በርካታ ዕድሎችን በማመቻቸት ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ዋና አሥተዳዳሪ ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የግጭትን ጉዳት መርምሮ የተረዳ፣ ለሰላም ዋጋ ከፍሎ መሥራት አያቅተውም” አቶ ይርጋ ሲሳይ
Next articleበደሴ እና አካበቢዋ ባለው የአየር ፀባይ ምክንያት ዛሬ እና ነገ በረራዎች አይኖሩም።