
ሰቆጣ: ታኅሣሥ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መሪዎች በተገኙበት “ሁሌም ለሰላም ዘብ እንቆማለን” በሚል መሪ መልዕክት ከሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ጋር የሰላም ውይይት ተካሂዷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የጽንፈኛውን ዕድሜ ያስረዘሙት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሁለት ገጽ ያላቸው ግለሰቦች መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
ይህንንም ለይቶ በማውጣት የጽንፈኛውን ዕድሜ ማሳጠር እንደሚገባ ነው አጥብቀው የገለጹት።
እርስ በርስ በሚደረጉ ጦርነቶች ምክንያት እናቶች ጥቁር ልብስ ለብሰው ቅጥ ያጣ ሀዘን ውስጥ እንደሚገኙም አንስተዋል። ከዚህ ችግር መዳን የሚቻለው ደግሞ በውይይት እንደኾነ ተሳታፊ እናቶች ተናግረዋል።
ጦርነት ሲመጣ ከእናቶች በላይ ጉዳት የሚያስተናግድ የለም ያሉት አስተያየት ሰጭዎቹ ከዚህ ችግር ለመውጣት እናቶች የሰላም ዘብ ለመኾን ግንባር ቀደም መኾን አለብን ነው ያሉት።
በአፈ ሙዝ መፎካከር ትርፉ ሞት እና ውድቀት መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ሹመት ጥላሁን ናቸው።
“ሰላም ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ የጋራ ድል እንደኾነ ያነሱት ምክትል አሥተዳዳሪው ይህንንም የጋራ ድል ማስቀጠል የሚቻለው የተጀመሩ የሰላም ስምምነቶችን መደገፍ ሲቻል ነው ብለዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሥራ ኀላፊ የኾኑት ሌትናል ጄኔራል አሰፋ ቸኮል ችግሮች ሁሉ መፍትሄ አልባ እንዳልኾኑ ገልጸዋል። ለዚህም ነው በጋራ ተነጋግረን ችግሮችን ለመፍታት በጋራ የመከርነው ብለዋል።
በዋግ ኽምራ በተደረጉ ውይይቶችም የሕዝቡን ጽናት እና ለሰላም ያለውን ቁረጠኛነት ማወቅ ችለናል ያሉት ጄኔራሉ ይህንን አንድነት አጽንተው እንዲያስቀጥሉም አሳስበዋል።
የሀገሪቷን ከፍታ ለማስቀጠል ትውልዱ ታሪክ አዋቂ አባቶችም ታሪክ ነጋሪ ከኾኑ ባለወደቧን ኢትዮጵያ በቅርቡ እውን ማድረግ እንድንችል ያግዘናል ነው ያሉት ጄኔራሉ።
በዋግ ኽምራ በድሃና ወረዳ፣ በጋዝጊብላ ወረዳ እና በስሃላ ሰየምት ወረዳ የሰላም ውይይት የተካሄደ ሲኾን በሰቆጣ ከተማ የተካሄደው የሰላም ምክክርም ሕዝባዊ አንድነትን ባጠናከረ መልኩ ተጠናቋል።
ዘጋቢ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
