
ደብረ ማርቆስ: ታኅሣሥ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች” በሚል መሪ መልዕክት በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር በአራቱም ክፍለ ከተሞች ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በብልጽግና ፓርቲ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መልካሙ ሽባባው የከተማዋን እና የአካባቢውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ኅብረተሰቡ አጋዥ መኾን አለበት ብለዋል።
የተጀመሩ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ እና ኅብረተሰቡ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲኾን የተጀመሩ ሕግን የማስከበር ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
የኅብረተሰቡ የሰላም እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ከመንግሥት ጎን ኾኖ መሥራት ይጠበቃልም ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የክፍለ ከተማ መሪዎች ልማትን ለማፋጠን እና የልማቱ ተጠቃሚ እንዲኾን ኅብረተሰቡ ሰላም ላይ አተኩሮ መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች እና እየተገነቡ የሚገኙ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስለመኾናቸው አስገንዝበዋል፡፡
የውይይት መድረኩ ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እና ሰላምን ለማጽናት በሚደረገው ርብርብ ላይ ኅብረተሰቡ ባለቤት እንዲኾን የሚያስችል ስለመኾኑም አብራርተዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ከሁለት ዓመታት በላይ የተሻገረው ግጭት ካደረሰው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት በተጨማሪ በኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎቻቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ተናግረዋል።
የትኛውም ግጭት የሚቋጨው በውይይት እና ድርድር ነው ያሉት ነዋሪዎቹ መንግሥት እና ተፋላሚ ኀይሎች ችግሩን በውይይት በመፍታት ኅብረተሰቡ ማኅበራዊ እረፍት እንዲያገኝ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት።
እንደ ክልል ብሎም እንደ ሀገር የተጀመሩ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች አበረታች መኸናቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ የታቀዱ የልማት ሥራዎች እና ፕሮጀክቶች እውን እንዲኾኑ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ አስረድተዋል።
በየአካባቢያቸው የሚታየውን ሕገወጥነት ለመከላከል እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዙም አረጋግጠዋል፡፡
ዘላቂ ሰላምን እና ልማትን ለማረጋገጥ ኅብረተሰቡ በባለቤትነት ስሜት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ተጠይቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
