በሁመራ ከተማ በሌማት ቱሩፋት ሥራዎች የተሠማሩ ወጣቶች ውጤታማ መኾናቸውን ተናገሩ።

3

ሁመራ: ታኅሣሥ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኑሮ ውድነትን በመቀነስ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሠራ መኾኑን በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳደር አስታውቋል።

የዞኑ ከፍተኛ መሪዎች በሰቲት ሁመራ ከተማ አሥተዳደር የሌማት ትሩፋት ተግባራትን ተመልክተዋል። በዚህም የኑሮ ውድነትን በመቀነስ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው ሲሉ የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ተናግረዋል።

በከተማዋ የዶሮ ርባታ፣ የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል። በተከዜ ተፋሰስ ዙሪያ እየለማ የሚገኘው አትክልት እና ፍራፍሬ ገበያውን በማረጋጋት የጎላ ሚና ያለው መኾኑንም አንስተዋል።

የሌማት ትሩፋት ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ባለሙያዎች እና አሥተዳደሩ ክትትል እና ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል።

በከተማው ተደራጅተው በዶሮ ርባታ በመሰማራት ውጤታማ መኾናቸውን ወጣቶች ተናግረዋል። በ340 ሺህ ብር ካፒታል፣ በ2 ሺህ 700 ጫጩቶች ሥራ መጀመራቸውን የሚያስታውሱት ወጣቶቹ አሁን ላይ ካፒታላቸው 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር መድረሱን ገልጸዋል።

ወጣቶቹ አክለውም ከ9 ሺህ በላይ ዶሮዎች እንዳሏቸውም ተናግረዋል። በመኾኑም የገበያ ትሥሥር በመፍጠር ረገድ ሊታገዙ እንደሚገባም አንስተዋል።

ዘጋቢ፦ አምሳሉ አሞኘ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሁሉም ለሰላም እንዲቆም ጥሪ ቀረበ።