
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 18/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአካባቢው ማኅበረሰብ ዘመናዊ አሠራርን በመከተል በውስን መሬት የተሻለ ገቢ እንዲያገኝ የሚያስችሉ ምክረ ሀሳቦችና ግብዓት እያቀረበ መሆኑን እንጂባራ ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የግንባታ ምዕራፎች ከ4ኛ ትውልድ የሚመደበው እንጂባራ ዩኒቨርሲቲ ሲመሠረት ይዞታቸውን የለቀቁ አርሶ አደሮችን የኑሮ ጫና ለመቀነስ የሚያስችሉ አሠራሮችን መዘርጋቱን አስውቋል፡፡ ለአብነትም ከ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ 16 የልማት ተነሺ ወጣቶችን በዘመናዊ የዶሮ እርባታና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሰማሩ ማድረጉን ነው የገለጸው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ብርሃኑ በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን የአካባቢውን ማኅበረሰብ የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽሉ ተግባራትን የማከናወን ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በዚህም የልማት ተነሺ አረሶ አደሮች ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ የማቋቋም ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የአካባቢው ማኅበረሰብ ዘመናዊ አሠራርን በመከተል በውስን መሬት የተሻለ ገቢ እንዲያገኝ የሚያስችሉ ምክረ ሀሳቦችና ግብዓት እያቀረበ እንደሆነም ፕሮፌሰር ብርሃኑ አስታውቀዋል፡፡
በዘመናዊ ዶሮ እርባታና አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ወደ ሥራ እዲገቡ የተደረጉ ወጣቶች ውጤታማ እንዲሆኑና ለሌሎችም ልምድ መቅሰሚያ ማዕከል እንዲሆኑ ዩኒቨርሲቲው ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ የእድሉ ተተቃሚ ወጣቶችም ሙሉ ጊዜያቸውን በሥራ በማሳለፍ የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን የገቢ አቅም ለማሳደግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ