
ከሚሴ: ታኅሣሥ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን የአንፆኪያ ገምዛ ወረዳና በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የደዋጨፋ ወረዳ ሕዝቦች የተሳተፉበት ሕዝባዊ የምክክር መድረክ በአንፆኪያ ገምዛ ወረዳ መኮይ ከተማ ተካሂዷል። የውይይት መድረኩ የሁለቱን ሕዝቦች የጋራ ሰላም ለማጠናከር ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
በመድረኩ በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደጄኔ ልመንህ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሽ አለማየሁ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ እና ሌሎች የክልልና የሁለቱ ዞኖች ከፍተኛ መሪዎች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የሁለቱ አጎራባች ወረዳ ነዋሪዎች ለዘመናት በክፉና በደጉ በአብሮነት ሲኖሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
አሁንም ያላቸውን መልካም ግንኙነት ለማጠናከር በትብብር እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የሰሜን ሸዋ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኤሊያስ አበበ የተጀመረው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በማጠናከር በጋራ ወደመልማት መሸጋገር ይገባል ብለዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ አለማየሁ በሁለቱ አጎራባች አካባቢዎች በተሠራው የተቀናጀ ተግባር በቀጠናው ሰላም በመፍጠር በጋራ ወደመልማት መሸጋገር መቻሉን አስረድተዋል።
ቀጣናው በግጭት ምክንያት የሰው ሕይወት የሚጠፋበት ሳይኾን አትክልትና ፍራፍሬ እየተጫን ለሌሎች አካባቢዎችም የሚደርስበት እንዲኾን በጋራ እየሠራን ነው ብለዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ በቀጣናው ከዚህ በፊት በብሔርና በሃይማኖት ሽፋን የሚቀሰቀሱ ግጭቶችን ማስቀረት እንደተቻለ ጠቅሰዋል።
በቀጣይ የተቀናጀ ሥራ በመሥራት ቀጣናው በጋራ በመስኖ የሚለማበት እንዲኾንና በጋራ የተፈጥሮ ሃብት ሥራዎች የሚከናወኑበት ለማድረግ የሁለቱ ዞኖች መሪዎችና ሕዝቡ ተቀራርበው መሥራት ጀምረዋል ብለዋል።
የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ የተጀመረው የሰላም እንቅስቃሴ ዘላቂ እንዲኾን የሃይማኖት መሪዎችና ሽማግሌዎች ታጥቀው በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደሰላም እንዲመጡ ተደጋጋሚ ጥሪ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የሁለቱ ዞን መሪዎች እና ሕዝቡ ተቀራርቦ በመሥራት በቀጣናው ሰላም መፍጠር እንደተቻለ በሁሉም አጎራባች አካባቢዎች መመልከታቸውን ገልጸዋል።
የተጀመረው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ቀጠናውን በልማት ለማስተሳሰርም እየተሠራ ነው ብለዋል።
በቀጣይ አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠር ታጥቀው የሕዝብን ሰላም የሚያውኩ አካላት መንግሥት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ተጠቅመው ሕዝባቸውን ሊክሱ እንደሚገባም አስረድተዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
