
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ለተለያዩ የሕግ ባለሙያዎች፣ ለአጋር እና ባለድርሻ አካላት በተሻሻለው የፌዴራል የግብር አዋጅ እና የተጨማሪ እሴት ታክስ ዙሪያ ሥልጠና ሰጥቷል።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የታክስ ጉዳዮች አማካሪ እንግዳወርቅ ገዛኸኝ የአዋጁ ዋና ዓላማ ዝቅተኛ ማኅበረሰቡ ላይ ያለውን የግብር ጫና ለመቀነስ ያለመ ነው ብለዋል።
ከታክስ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ በር የሚከፍተውን የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ የሚገድብ እንደኾነም ገልጸዋል።
ታክስን ከማጭበርበር እና ከመሰወር ጋር ያሉ ጉዳዮችን የሚያርም ኾኖ አዋጁ ወጥቷልም ነው ያሉት። የግብር ከፋዮች ደረጃ በሦስት የተከፈለ መኾኑን ያነሱት አቶ እንግዳወርቅ በአዲሱ አዋጅ ግን ደረጃ ሀ እና ለ ተብለው እንደሚከፈሉም አንስተዋል።
አዋጁ በአዲስ የተካተቱ የዲጂታል ይዘት ፈጠራ እና የዲጅታል አገልግሎትን የተመለከቱ አንቀጾችንም ይዟል ብለዋል። የውጭ ሀገር ዜጎች በክልሉ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ከኾነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚሰጠው መረጃ መሠረት የሥራ ግብር የሚከፍሉበት አሠራር ተቀምጧል ብለዋል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኅላፊ እና የሕገ ወጥ ጸረ ኮንትሮባንድ ጥምር ግብረ ኃይል የወንጀል ጉዳዮች ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አያሌው አባተ (ዶ.ር) አዋጁ በቴክኖሎጂ የታገዘ የግብር ሥርዓት እንዲኖር እና የግብር ከፋዮችን ገቢ ያማከለ ሥርዓት እንዲኖር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኅላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) በበኩላቸው ትክክለኛ ግብር ከፋይ እና ትክክለኛ ነጋዴ ሕግን አክብሮ የሚንቀሳቀስ ግብር ከፋይ ነው ብለዋል።
የሚሰበሰበው ግብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው ያሉት ዶክተር መንገሻ የወጭ ፍላጎት እና የሕዝብ የመልማት ጥያቄም በዚያው ልክ እያደገ መኾኑን አንስተዋል።
ይሄን የሚመጥን ግብር ለመሰብሰብ አዋጆችን በአግባቡ ማጽደቅ እና ተግባራዊ ማድርግ፤ ሕገ ወጥነትንም በጋራ መከላከል ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በግብር አሰባሰብ ሂደት ከሌሎች ክልሎች ጋር ክልሉ ሲወዳደር የሚቀሩ ነገሮች አሉ ያሉት ቢሮ ኅላፈው አሁን ካለው በላይ መሥራት እንደሚጠይቅም አንስተዋል።
የግብር ጉዳይ የሁሉም ነው ያሉት ዶክተር መንገሻ ባለድርሻ እና አጋር አካላት እስካሁን ለተገኘው ውጤት ምስጋና ይጋባቸዋል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
