ከተሞች ወደ ዓለማቀፋዊ የከተማ ሥርዓት ጉዞ እያመሩ ነው።

5

አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አምስት ከተሞች ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር የዲጂታል አድራሻ ሥርዓትን ለማልማት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።

በአዲስ አበባ በተካሔደው የፊርማ ሥነ ሥርዓት የተካተቱት የወልድያ፣ የደብረ ታቦር፣ የደሴ፣ የደብረ ማርቆስ እና የከሚሴ ከተሞች ናቸው።

የየከተሞቹ ከንቲባዎች ከኢኒስቲትዩቱ ጋር የተፈራረሙት ምቹ እና ዘመናዊ ከተማ ለመገንባት፣ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት፣ ለመሬት አሥተዳደር እና ለቱሪዝም መረጃዎች እንዲሁም ለመሠረተ ልማት ግንባታ በቂ መረጃ መስጠት እንዲቻል የሚያደርግ መኾኑን በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።

የአማራ ክልል ከተማ ልማት ቢሮ ኀላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ.ር) ስምምነቱ “ከተሞቻችን ወደ ዓለማቀፍዊ የከተማ ሥርዓት ጉዞ የጀመሩበት ሁነት ተደርጎ ይወሰዳል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦ ስፔሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት የሲስተም ግንባታ፣ የዲጂታል ካርታ ዝግጅት እንዲሁም የከተሞች የመንገድ፣ የሰፈር ይዞታ እና የቤት ቁጥር ምዝገባን ያካትታል ብለዋል።

ይህ ሥርዓት ከጎግል ማፕ በተሻለ ፈጣን እና የከተሞችን ለውጥ መረጃወችን ከመስጠቱ ባሻገር አስተማማኝ እና በግለሰቦች የማይዘወር መረጃ እንዲኖር ያስችላል ነው ያሉት።

በትግበራ ወቅት ከተሞቹ እና ኢንስቲትዩቱ የሚሠራቸው ተግባሮች እና የበጀት ምንጮችም ተለይተዋል ብለዋል።

ዘጋቢ:- አንዷለም መናን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተደራጀ እውቀት እና አሠራር ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋል።
Next articleየተሻሻለው የገቢ ግብር አዋጅ የግብር ከፋዮችን ገቢ ያማከለ ሥርዓት እንዲኖር ትልቅ ሚና ያለው ነው።