የተደራጀ እውቀት እና አሠራር ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋል።

6

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አንከሻ ጓጉሣ ወረዳ ማንጃ ተንኮሻ ቀበሌ በኩታ ገጠም እየለማ የሚገኝ የስንዴ ሰብል ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አዲሱ መሐመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የማንጃ ተንኮሻ ቀበሌ አርሶ አደሮች በበጋ ስንዴ ልማት ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል። የግብርና ባለሙያዎች ተከታታይ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸውም ገልጸዋል። በቀበሌዋ 450 ሄክታር መሬት በስንዴ ኩታገጠም እየለማ መኾኑም ተመላክቷል።

አርሶ አደር ብርሃኔ አየነ የኩታገጠም ልማት አዋጭ መኾኑን ተናግረዋል። ከ2015 ዓ.ም ጀምረው በኩታገጠም ስንዴ እያለሙ መኾናቸውን አንስተዋል። የስንዴ ልማት ተጠቃሚ እያደረጋቸው እንደኾነም ገልጸዋል። የበለጠ ተጠቃሚ እንዲኾኑ መንግሥት የመስኖ አቅሙን በግድብ እንዲያጠናክራላቸው ጠይቀዋል። የመስኖ አቅሙ ከተጠናከረ ከዚህ በላይ ተጠቃሚ እንኾናለን ነው ያሉት።

ሌላኛው አርሶ አደር ጌታሁን ቢተው የስንዴ ምርት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል። የግብርና ባለሙያዎች ባስተማሩን መሠረት ተጠቃሚ እየኾን ነው ብለዋል። የበለጠ ተጠቃሚ እንዲኾኑ በቂ ግብዓት በወቅቱ እና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብም ጠይቀዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ከመጀመሩ አስቀድሞ በባሕላዊ መስኖ የመጠቀም ልምድ እንዳላቸው ተናግረዋል። እየለማ ያለው ማሳ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው የስንዴ ልማት ዳቦ ብቻ አይደለም፤ ስንዴ ራስን ከተረጅነት ማላቀቅ እና ሉዓላዊነት ነው ብለዋል። ይሄን ታሳቢ በማድረግ ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ትኩረት ተሰጥቷል ነው ያሉት።

የግብዓት አቅርቦት እና ሌሎች ሥራዎችን በውጤታማነት ለመፈጸም ስንዴን ከተቆራረጠ እርሻ ወደ ኩታገጠም እርሻ የመቀየር ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።

በአንከሻ ጓጉሣ ወረዳ ማንጃ ተንኮሻ ቀበሌ ስንዴ በውጤታማነት እየተተገበረ መኾኑን ገልጸዋል። የአካባቢውን ጸጋ በመለየት የተሻለ ሥራ ተሠርቷል፤ ነገር ግን ከዚህ በላይ መጠቀም እና የአርሶ አደሮችን የኢኮኖሚ አቅም ማሳደግ ያስፈልገናል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በአማራ ክልል ለመስኖ ልማት ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል። በመስኖ ከሚታረሰው መሬት ደግሞ ለስንዴ ልማት ትኩረት መሰጠቱን ነው የገለጹት።

የበጋ መስኖ ልማት ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አንከሻ ጓጉሣ የጎበኙት የኩታገጠም የስንዴ ልማት ትምህርት የሚወሰድበት መኾኑን ገልጸዋል።

የሚታረሰውን መሬት እያሰፉ ምርትና ምርታማቸውን እያሳደጉ መኾናቸውን ተናግረዋል። ይህ ደግሞ ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተሰጠው ትኩረት እያደገ መምጣቱን ያሳያል ነው ያሉት።

አርሶ አደሮች በተሟላ ግንዛቤ እና ተግባቦት እየተገበሩ መኾናቸውን አረጋግጠናል ብለዋል። የአርሶ አደሮች ግንዛቤ ማደጉንም ገልጸዋል። የግብዓት አቅርቦት የተሻለ መኾኑን ተናግረዋል።

በስንዴ ልማቱ አሠራር፣ አመለካከት፣ እውቀት እና መሬት ተቀናጅተው አይተናል ብለዋል። የተደራጀ እውቀት እና አሠራር ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድግ መኾኑን ተናግረዋል። በአካባቢው የታየውን መልካም ተሞክሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ማስፋት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኮሪደር ልማት ለነባር ከተሞች አዲስ ገጽታን ፈጥሯል።