
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ በስሩ 142 ከተሞችን በአባልነት አቅፏል። ከተሞች አንዱ ከሌላው ያላቸውን ተሞክሮ እንዲለዋወጡ እያደረገ ይገኛል።
በዚህ ዓመትም በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት የኢትዮጵያ ከተሞች የኮሪደር ልማት አተገባበርን በተመለከተ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱም የኮሪደር ልማት ለከተሞች አዳዲስ ገጽታ እያሳየ መኾኑ ተነስቷል። የድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር የኮሪደር ልማት አሥተባባሪ የወንድወሰን ጀምበሬ የኮሪደር ልማት ከተማውን በአዲስ የገነባ መኾኑን ያነሳሉ።
ድሬዳዋ ከተማ ጥንታዊ ከመኾኗ ጋር ተያይዞ የመንገድ ግንባታዎች ተሽከርካሪ ተኮር እንደነበሩ አንስተው በኮሪደር ልማት የመንገዱን ገጽታ የመቀየር እና የመዝናኛ ቦታዎችን የመክፈት ሥራዎች መሠራታቸውን አስታውቀዋል። የቆዩ መንገዶችንም በአዲስ የመቀየር ሥራ እንደተከናወነ መኾኑን አንስተዋል።
በተመሳሳይ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ የኮሪደር ልማት ለደብረ ማርቆስ ከተማ የተሻለ ገጽታ የፈጠረ መኾኑን አንስተዋል።
በደብረ ማርቆስ ከተማ በዋና ዋና የከተማው መንገዶች ኮሪደር ልማት እየተገነባ መኾኑን አስታውቀዋል። የኮሪደር ልማቱም ለከተማው አዲስ ገጽታ የፈጠረ መኾኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ዋና ዳይሬክተር አንዷለም ጤናው መድረኩ ለከተሞች መማማሪያ በመፍጠር ተልዕኳቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲቻል የተዘጋጀ መኾኑን አስረድተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
