
ደብረ ብርሃን: ታኅሣሥ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለዘላቂ ሰላም እና ልማት የወጣቶች ሚና” በሚል መሪ መልዕክት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና ልማት እንዲፋጠን ወጣቶች የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ወጣቶች በከተማዋ ችግር በገጠመ ጊዜ ከመንግሥት ጎን በመቆም ለልማት እና ለሰላም ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ መሳለጥ አጋዥ ናቸው ብለዋል።
የተጀመሩ የሰላም እና የልማት ሥራዎች ዘላቂ እንዲኾኑ ወጣቶች የሚጠበቅባቸውን ሚና አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አቶ በድሉ አሳስበዋል። መንግሥትም የጀመረውን የወጣቶች ተጠቃሚነት የማሳደግ ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ወጣቶች የአንድ ሀገር የጀርባ አጥንት ናቸው ብለዋል። ወጣቱን በአግባቡ በማደራጀት ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ እና ለሀገር እድገት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ መሥራት ይጠበቃልም ነው ያሉት።
በክልሉ ባጋጠመው የሰላም እጦት ወጣቶች ያልተገባ ዋጋ እየከፈሉ መኾኑን ያነሱት ዶክተር ሙሉነሽ ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በሰላም እጦቱ የአማራ ሕዝብ ነባር እሴቶች እየተሸረሸሩ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
መንግሥት የአማራ ሕዝብ ሁለንተናዊ ጥያቄዎች በሠለጠነ አግባብ እና በውይይት እንዲፈቱ በትኩረት እየሠራ እንደኾነም አብራርተዋል። በዚህ ዘመን “ልዩነቶች መፈታት ያለባቸው በጦርነት ሳይኾን በሀሳብ የበላይነት ብቻ ሊኾን እንደሚገባውም” ተናግረዋል።
አሁን ላይ በተሳሳተ መንገድ ወደ ጫካ የገቡ ወገኖች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ እየተቀበሉ ወደ ቀደመው ሰላማዊ ሕይወት እየተመለሱ መኾኑንም ዶክተር ሙሉነሽ ተናግረዋል፡፡ የክልሉ መንግሥትም ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመተባበር የቀድሞ ታጣቂዎችን የማቋቋም ሥራ እያከናወነ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ደብረ ብርሃን ከተማ ሰላም ወዳድ፣ ልማት ናፋቂ ወጣቶች ያሉባት ከተማ መኾኗን ያነሱት ዶክተር ሙሉነሽ ይህንን ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ወጥና ትንሳኤዋን እያበሰረች መኾኑን ያነሱት ዶክተሯ ወጣቶች በፖለቲካው፣ በማኅበራዊ እና በምጣኔ ሃብት ዘርፉ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት በትጋት እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይት መድረኩ የክልል እና የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎችን ጨምሮ ከከተማው ሁሉም ቀበሌዎች የተውጣጡ ወጣቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ዘጋቢ:- ደጄኔ በቀለ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
