
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አመልድ ኢትዮጵያ ነባር የቤተክርስቲያን ደኖችን መሠረት ያደረገ የመልክዓ ምድር መልሶ ማልማት ክልል አቀፍ አውደ ጥናት በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ በክልሉ እየተመናመነ የሚገኘው የደን ሃብት ልማት በተለይ የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ለማድረግ እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ኑሮ እንዲሻሻል አመልድ ኢትዮጵያ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
“የሃይማኖት አባቶች ደኖች እንዲጠበቁ በሚሠሩት ሥራ ትልቅ ባለውለታዎች ናቸው” ነው ያሉት።
እስካሁን ባለው ቤተክርስቲያን እና የተለያዩ የልማት ድርጅቶች በሠሩት ተግባር በክልሉ 18 ነጥብ 9 በመቶ የሚኾን የደን ሽፋን ተደርሷል ብለዋል።

በቀጣይም በአካባቢያችን ያሉ የተራቆቱ መሬቶችን ምርታማነታቸው እንዲሻሻል ለማድረግ፣ ለማኅበረሰቡ አማራጭ የገቢ አቅም እንዲፈጥር፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጥር እና እየፈተነን ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም እንዲያስችል እነዚህን ጥብቅ ደኖች መንከባከብ እና መጠበቅ እንዲሁም ማልማት የሁሉም ድርሻ መኾን አለበት ነው ያሉት።
በአውደ ጥናቱ በቤተክርስቲያን ደኖች ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ጽሑፋቸውን እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።
ዘጋቢ:-ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
