የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚገኙ ከ80 በመቶ በላይ ሆቴሎች በአብዛኛው ሥራ ማቆማቸውን መንግሥት አስታወቀ፡፡

133

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 18/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኮሮና ቫይረስ በኢንቨስትመንት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቋቋም ድጋፍ እያደረገ መሆኑን መንግሥት አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ ባለሀብቶች ዓለማቀፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች መዳከምን በመቋቋም በድሕረ ኮሮና ቫይረስ በፍጥነት በማገገም የኢንቨስትመንትና የማምረት እንቅስቃሴዎችን እንዲቀጥሉ እንደሚደግፍም አስታውቋል፡፡ የመጀመሪያው ድጋፍ የፋይናንስ ድጋፍ ነው ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለሀብቶችን ለመደገፍ 15 ቢሊዮን ብር ይፋ አድርጓል፡፡ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትም እያመቻቸ መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡ መንግሥት በሁለተኛ ደረጃ የትግበራ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቋል፡፡ በዚህ ረገድም አስመጭና ላኪ ባለሀብቶችን ለመደገፍ በሎጂስቲክ ዘርፍ የተለያዩ የሀገር ውስጥ የታሪፍ ማሻሻያና ቅናሽ ተደርጓል ነው የተባለው፡፡

ባለሀብቶች የግብር ቅነሳ፣ ድጎማ፣ የፋይናንስ ተደራሽነትና ተጨማሪ የሥራ አፈጻጸም ድጋፍ እንደሚያነሱ የገለጸው መንግሥት በቅርብ ምክክር በማድረግ ባለሀብቶች ያነሱትንና ተጨማሪ እርምጃዎችን ከግምት በማስገባት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ነው ያስታወቀው፡፡ የኮሮና ቫይረስን ጫና እያጠናና እየተከላከለ በድህረ ኮሮና ቫይረስ መልሶ ማገገም አስፈላጊ የፖሊስ እርምጃዎችን በመለዬት ላይ እንደሆነም አስታውቋል፡፡ መንግሥት ዛሬ እንዳስታወቀው ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገባው ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በአማካይ 50 በመቶ በማደግ ላይ ነው፡፡ በ2010 ዓ.ም ደግሞ 4 ነጥብ1 ቢሊዮን ከፍታ ደርሷል ነው ያለው፡፡ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ቀዳሚ፣ በአፍሪካ ደግሞ አምስተኛ ደረጃን ይዛለች ነው የተባለው፡፡

ይህን ለማስቀጠልም ካለፈው ዓመት ጀምሮ የሀገሪቱን የኢንቨስትመንትና የንግድ ከባቢ ሁኔታ ለማሻሻል የታቀዱ ተከታታይ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ወደ ትግበራ ገብተዋል ተብሏል፡፡ በዚህ ጠንካራ የእድገት መሠረት በዘንድሮ ዓመትም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከፍ እንደሚል ቢገመትም ኮሮና ቫይረስ አስተጓጉሎታል ነው የተባለው፡፡ ዓለም አቀፍ ትንተናዎችን መሠረት አድርጎ መንግሥት እንደገለጸው በ2012/13 የዓለም አቀፍ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከ30 እስከ40 በመቶ እንደሚቀንስ ተገምቷል፡፡ ይህ ጫናም በኢትዮጵያ ላይ እንደሚንጸባረቅ ነው የተገለፀው፡፡

የኮሮና ቫይረስ በፍላጎት፣በአቅረቦትናበፋይናንሱ ላይ ጫና እንደሚኖረውም መንግሥት አስታውቋል፡፡ ይህ ጫና ቢኖርም ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ላይ እንደሚገኙም መንግስት አስታውቋል፡፡ ከመድሃኒት ምርቶችና ከግብርና ጋር የተዛመዱ የኢንቨስትመንት ፍላጎቶች አሁንም ከፍተኛ መሆናቸውንም አስታውቋል፡፡ ለዚህም መንግስት አዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮችን እንደሚያስተዋውቅ ነው የገለጸው፡፡

የጨርቃጨርቅና የአልባሳት ዘርፎች ችግር የሚገጥማቸው ስለሚሆኑ መንግሥት ያሉትን ድጋፎች ያደርጋል ነው ያለው፡፡ የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ የቱሪዝም ዘርፉ ክፉኛ እየተጎዳ እንደሆነ የገለጸው መንግሥት ለአብነት በአዲስ አበባ የሚገኙ 80 በመቶ በላይ ሆቴሎች ሥራቸውን በአብዛኛው ማቆማቸውን ጠቅሷል፡፡ ቫይረሱ እስከ2013 ድረስ የዘርፉን እድገትና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን እንደሚያቀዘቅዝም ተገምቷል፡፡ ከፍተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን እንደሳበ የተነገረለት የአበባ ምርት ነው፤ ይህም ሆኖ የቫይረሱ ተጽዕኖ የአበባ ፍላጎት ላይ ጫና ማሳደሩም ተጠቁሟል፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleመለስተኛ የዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካዎችን በሁሉም ክልሎች ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ገለጹ፡፡
Next articleበምዕራብ ጎንደር ዞን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰሊጥ ምርት ለማግኘት ታቅዷል፡፡