ኤች አይ ቪ ኤድስ አሁንም ትኩረትን ይሻል።

35
ወልድያ: ታኅሣሥ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ሥርጭት መከላከል እና ቁጥጥር ላይ ያተኮረ ምክክር ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።
የመምሪያው የኤች አይ ቪ ዘርፈ ብዙ ምላሽ አሥተባባሪ ሰኢድ ይማም በከተማ አሥተዳደሩ የኤች አይቪ ኤድስ ቫይረስ ሥርጭት ባልተለመደ ሁኔታ እያሻቀበ መኾኑን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ 6 ሺህ 171 አዋቂ እና 96 ሕጻናት በጥቅሉ 6 ሺህ 267 ሰዎች መድኃኒት የሚወስዱ መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ከሐምሌ እስከ ኅዳር 2018 ዓ.ም ባሉት አምስት ወራት ውስጥ 13 ሺህ 515 ሰዎች ተመርምረው 112 ሰዎች የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው ተገኝቷል ነው ያሉት።
ይህ ቁጥር ወደ ጤና ተቋም መጥተው የተመረመሩ እና ክትትል የሚያደርጉ ወገኖች ናቸው ያሉት ሰኢድ ይማም ያልተመረመሩ እና ራሳቸውን ደብቀው የሚኖሩ ወገኖች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችልም አሳስበዋል።
ሥርጭቱን ለመቆጣጠር በሴተኛ አዳሪዎች፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ኮሌጆች ላይ ትኩረት በማድረግ የአቻ ለአቻ ውይይት እየተካሄደ መኾኑን ገልጸዋል።
ሌሎች አደረጃጀቶችን በመጠቀምም የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተከናወነ ቢኾንም የሥርጭት መጠኑ ተጨማሪ ሥራ እንደሚጠይቅ አመላካች ነው ብለዋል።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሲስተር ረቂቅ መንግሥቴ ወልድያ ከተማ የወደብ መዳረሻ እና መተላለፊያ በመኾኗ እና የበሽታው ሥርጭት እንዲስፋፋባት ምክንያት መኾኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ለኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ሥርጭት የሚሰጠው ትኩረት የተዘነጋ እስኪመስል ድረስ ችላ መባሉንም ጠቁመዋል።
ሥርጭቱን ለመግታት የኅብረተሰብ ልዩ ልዩ መዋቅር ላይ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ሲስተር ረቂቅ የሃይማኖት አባቶች እና የእድር መሪዎች ሚናቸው ጉልህ መኾኑን አንስተዋል።
የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የግሉ ዘርፍ እና ሲቪክ ማኅበራት እንዲሁም የሚዲያ አካላት ግንዛቤ ፈጠራ ላይ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የምክክሩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሃይማኖት ተቋማት እና መሰል ማኅበራዊ መዋቅሮች ስለ ጉዳዩ ሲያነሱ አይስተዋልም፤ ቅስቀሳው እጅግ በጣም ተቀዛቅዟል ብለዋል።
የበሽታው ሥርጭት እና ቁጥር በምክክር መድረኩ ስንሰማ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መኾኑን ተገንዝበናል ብለዋል። ይህንን ሀሳብ በየመዋቅራችን የማስገንዘብ ግዴታ እንዳለብን ተረድተናል ነው ያሉት።
የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የትምህርት ቤት መሪዎች፣ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸው ወጣቶች፣ ማኅበራት እና ሌሎች የሲቪክ ማኅበር አደረጃጀቶች በምክክሩ ተሳትፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ጦርነት በቃ ሊባል ይገባል” ወረኢሉ ነዋሪዎች
Next articleየሃይማኖት አባቶች ደኖች እንዲጠበቁ በማድረግ በኩል ትልቅ ባለውለታዎች ናቸው።