
ደሴ: ታኅሣሥ 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳደር በወቅታዊ የሰላም እና የፀጥታ ጉዳይ ከወረኢሉ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ምክክር አካሂዷል።
በውይይቱ የተሳተፉት የወረዳው ነዋሪዎች የሰላም እጦቱ ልጅን ያለወላጅ፣ ወላጅን ያለ ጧሪ ቀባሪ፣ ሕዝባችን ያለጥሪት እንዲቀር እያደረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በግጭቱ እየደረሰ ያለው ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ ፆታዊ ጥቃት እና ቁሳዊ ውድመት ጊዜው በተራዘመ ቁጥር ጉስቁልናን በማስከተል አንገታችንን እንድንደፋ የሚያደርግ በመኾኑ በቃ ሊባል ይገባል ብለዋል።
የሕዝቦች ጥያቄ የሚመለሰው በመፈቃቀድ እና በሰጥቶ መቀበል መርሕ እንዲኾን እና ሰላማችን እንዲመለስልን እንፈልጋለን ብለዋል።
ነዋሪዎቹ አክለውም ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርገው ሕዝብን በመውደድ እና ለሕዝብ ፍላጎት ቅድሚያ በመስጠት እንደኾነ አንስተዋል።
ታጣቂዎችም የመንግሥትን የሰላም አማራጭ በመቀበል ቀርቦ ለመነጋገር ዝግጁ እንዲኾኑ ጠይቀዋል።
የወረኢሉ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ደለለኝ ቸርነት ጫካ የገቡ ኀይሎች በአካባቢው ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን አስከትለዋል ነው ያሉት።
አሁን ላይ በአንፃራዊነት የሰላም አየር እየተነፈስን ቢኾንም የተሟላ ሰላም እንዲሰፍን እና የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ማኅበረሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ ዳኛው የሰላም እጦቱ እንዲራዘም የኾነው ጫካ የገቡት አካላት ማኅበረሰቡን እንደ መደበቂያ ተጠቅመው ለቡድኑ የሚሠሩ ግለሰቦች በመኖራቸው እንደኾነ አስረድተዋል።
መንግሥት የዘረጋው የሰላም አማራጭ ተጠቅመው እንዲገቡ በየቀበሌው ያሉ ታጣቂዎችን በመለየት መክራችሁ ልትመልሱ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ ፦ አንተነህ ፀጋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
